
የባንኩ ሌላ ሰራተኛ ከዚህ በፊት 900 ሚሊዮን ዶላር በስህተት ልኮ ነበር
መቀመጫውን በዓለማችን ቁጥር አንድ የዲፕሎማሲ ማዕከል ኒውዮርክ ያደረገው ሲቲ ባንክ ከሰሞኑ አነጋጋሪ ድርጊት ፈጽሟል፡፡
የባንኩ አንድ ደንበኛ 280 ዶላር ለማስላክ በአካል መምጣቱን ተከትሎ የባንኩ አንድ ሰራተኛም አገልግሎቱን ይሰጣል፡፡
ይሁንና ይህ የባንክ ባለሙያ በስህተት በርካታ ዜሮ ቁጥሮችን በመንካት በጠቅላላው 81 ትሪሊዮን ዶላር ያስተላልፋል፡፡
ሂሳቡ እንዲዘዋወር መፍቀድ የነበረበት ሌላኛው የባንክ ሰራተኛም ትኩረት ሳያደርግ የመጀመሪያው ባለሙያ የሰራውን ስህተት አሳልፎታል ተብሏል፡፡
ገንዘቡ ቢተላለፈው ግለሰቡን ባንድ ጊዜ የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ የሚያደረገው ነው፤ ከኢለን መስክን ጠቅላላ ሀብት በ200 እጥፍ የሚልቅ ሀብት ባለቤት ያደርገው ነበር።
የገንዘብ ዝውውሩን የሚያጸድቀው ሶስተኛው እና የመጨረሻው ባለሙያ ግን እንደ ቀልድ ሊያሳልፈው ሲል ማየቱን ተከትሎ ባንኩ ከኪሳራ መዳኑን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ይህ ባንክ ባሳለፍነው የፈረንጆቹ 2024 ዓመት ውስጥ 10 ጊዜ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ በስህተት አስተላልፎ ነበር፡፡
ባንኩ በ2023 13 ጊዜ በስህተት ገንዘብ ልኮ የነበረ ሲሆን ከአምስት ዓመት በፊት ደግሞ 900 ሚሊዮን ዶላር በስህተት ከላከ በኋላ ገንዘቡ በህግ ክርክር ከተደረገበት በኋላ ገንዘቡ ቢመለስም የባንኩ ስራ አስኪያጅ ስራቸውን ማጣታቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የሲቲ ባንክ አጠቃላይ ሀብት 150 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ሲሆን ከሰሞኑ የባንኩ ባለሙያ በስህተት ሊልከው የነበረው ገንዘብ ግን ከዚህ በጣም ብዙ እጥፍ የሚበልጥ ነበር ተብሏል።