የጣፊያ ህክምና ለማግኘት ወደ ሆስፒታል የገባው ታካሚ በስህተት የወንድ የዘር ፍሬ ቱቦውን አጣ
ግለሰቡ የቀዶ ጥገና ሐኪሞቹ ሳያጣሩ ለመሃንነት ዳርገውኛል ሲል ገልጿል
ስህተቱን የፈጸሙት ሐኪሞች ሃላፊነት ከመውሰድ ይልቅ በሳይንሳዊ መንገድ የልጅ አባት እናደርግሃለን እንዳሉት ተጎጂ ተናግሯል
የጣፊያ ህክምና ለማግኘት ወደ ሆስፒታል የገባው ታካሚ በስህተት የወንድ የዘር ፍሬ ቱቦውን አጣ፡፡
የ41 ዓመቱ አርጀንቲናዊ ጆርጅ ባሴቶ በጣፊያው ላይ የቀዶ ሕክምና ለማድረግ ነበር ወደ ሆስፒታል ያመራው፡፡
የአርጀንቲናዋ ፍሎሬንሲዮ ዲያዝ ግዛት ነዋሪው ይህ ግለሰብ በቀጠሮው መሰረት ወደ ሆስፒታል ቢያመራም አስደንጋጭ የሕክምና ስህተት እንደተፈጸመበት ተናግሯል፡፡
የቀድ ሕክምና ሐኪሞች ቡድን የሕክምና ዝርዝር መረጃዬን ሳያዩ በቀጥታ በፍጥነት ወደ ቀዶ ሕክምና ክፍል መወሰዱን ያስታውሳል፡፡
ከተሰጠው የማደንዘዣ መድሃኒት ሲነቃ ያልሆነ ቦታ ህመም ሲሰማው ምን እንደተካሄደ ሐኪሞችን ሲጠይቅ የወንድ የዘር ፍሬ መፍሰሻ ቱቦው እንደተቆረጠ ይነገረዋል፡፡
በግለሰቡ ላይ በተፈጸመበት ስህተት ምክንያት በተፈጥሯዊ መንገድ ልጅ መውለድ እንደማይችልም ተነግሮታል፡፡
የሚፈልገው ሕክምና ይህ እንዳልነበር በወቅቱ በስራ ላይ ለነበሩ ሐኪሞች መናገሩን ተከትሎ በተደረገው ማጣራት የሕክምና ስህተት እንደተፈጸመበት በሆስፒታሉ ይነገረዋል፡፡
ስህተቱን የፈጸሙት ሐኪሞችም ለሰሩት ስህተት ሐላፊነት ከመውሰድ ይልቅ በተደጋጋሚ በሳይንሳዊ መንገድ ልጅ እንድትወልድ ማድረግ እንችላለን እንዳሉት ለመገናኛ ብዙሃን ቃለ መጠይቅ አድርጓል፡፡
ይሁንና ግለሰቡ ካለው የጤና ሁኔታ፣ እድሜ እና ሌሎች ምክንያቶች ልጅ የመውለድ እድሉ እጅግ የመነመነ ነው ሲል ለየት ያሉ ዘገባዎችን በመስራት የሚታወቀው ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡
የሁለት ወንድ ልጆች አባት ነው የተባለው ይህ ግለሰብ አዲስ የፍቅር ግንኙነት እንደመሰረተ እና ተጨማሪ ልጆችን የመውለድ እቅድ ነበረውም ተብሏል፡፡
ስህተቱን የሰራው ሆስፒታል በበኩሉ የሕክምና ስህተቱ የተፈጸመው ታካሚው ወደ ሆስፒታላችን የመጣበት ዕለት የዘር ፍሬ ቱቦ ቀዶ ህክምና የምናደርግበት ቀን በመሆኑ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
ሰህተቱን የፈጸሙት ሐኪሞች እና ሆስፒታሉ ላይ ክስ እንደሚመሰርት የተናገረው ይህ ግለሰብ ስህተቱ ከባድ ቸልተኝነት እና ሊቀለበስ የማይችል መሆኑንም ተናግሯል፡፡