ቡርኪናፋሶ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን የሚከለክል ረቂቅ ህግ አወጣች
የሀገሪቱ ፍትህ ሚኒስቴር ግብረሰዶማዊነትና ተያያዥ ተግባራት የተከለከሉና በወንጀል የሚያስጠይቁ ናቸው ብሏል
ኡጋንዳ እና ጋና መሰል ህጎችን ማውጣታቸው ይታወሳል
የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ ጁንታ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን የሚከለክልና በህግ ተጠያቂ የሚያደርግ ረቂቅ ህግ አወጣ።
በኢብራሂም ትራወሬ የሚመራው የሚኒስትሮች ምክርቤት ሳምንታዊ ስብሰባውን ሲያደርግ በረቂቅ የቤተሰብ ህግ ላይ መክሯል።
በዚህም የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ወደ ስራ እንዲገባ ወስኗል ነው የተባለው።
የሀገሪቱ ጊዜያዊ የፍትህ ሚኒስትር ኢዳሶ ሮድሪክ ባያላ፥ “ከዛሬ ጀምሮ ግብረሰዶማዊነትና ተያያዥ ተግባራት የተከለከሉና በወንጀል የሚያስጠይቁ ናቸው” ማለታቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
የሚኒስትሮች ምክርቤት ያጸደቀው ረቂቅ ህግ ወደ ስራ እንዲገባ በፓርላማ መጽደቅና የሀገሪቱ የሽግግር ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ትራወሬ ለህዝብ ይፋ ሊያደርጉት ይገባል።
የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ከ2022 ጀምሮ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን በያዙ መሪዎች እየተመራች ነው።
ጎረቤቶቿ ማሊ እና ኒጀርም በተመሳሳይ መንግስት በገለበጡ ወታደሮች እየተመሩ ሲሆን፥ ሶስቱም ሀገራት ምርጫ ማካሄድ አልቻሉም።
ሀገራቱ ከምዕራባውያን ይልቅ ፊታቸውን ወደ ሩሲያ በማዞርም የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው።
ቡርኪናፋሶ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻና ግብረሰዶምን ከከለከሉት ኡጋንዳ እና ጋና ጎራ ተሰልፋለች።
ምዕራባውያን ባህልና እምነታችን በርዘዋል ያለችው ኡጋንዳ ባለፈው አመት ግንቦት ወር የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን የሚከለክልና እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት የሚደነግግ ህግ ማውጣቷ ይታወሳል።
ህጉን ተከትሎ የአለም ባንክ ለካምፓላ ብድር በመከልከሉም፥ ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ “የዓለም ባንክ ባህላችንን እና ሀይማኖታችንን በገንዘብ እንድንቀይር እያስገደደን ነው" በማለት የባንኩን ውሳኔ መቃወማቸው አይዘነጋም።
ጋናም በያዝነው የፈረንጆቹ አመት የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ ፈጻሚዎችን በወንጀል ተጠያቂ የሚያደርግ ህግ ማጽደቋ የሚታወስ ነው።