
ትራወሬ ወታደራዊው መንግስት በግንቦት ወር እስከ ቀጣዮቹ አምስት አመታት ሀገሪቱን መምራቱን እንደሚቀጥል መወሰናቸው ይታወሳል
የቡርኪናፋሶ ጁንታ የሀገሪቱን ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር አፖሊኒየር ጆቺም ኬለም ደ ታምቤላ ከስልጣናቸው አነሳ።
የኢብራሂም ትራወሬ ጽህፈት ቤት በመስከረም ወር 2022 የተሾሙት ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተባረሩበትን ምክንያት አልጠቀሰም።
ወታደራዊ ጁንታው የሀገሪቱን መንግስት መበተኑንም ነው ትናንት ባወጣው ድንጋጌ ያመላከተው።
መንግስት ቢፈርስም ሚኒስትሮች አዲስ ካቢኔ እስኪሾም ድረስ በስራቸው ላይ ይቆያሉም ብሏል።
ተደጋጋሚ የመንግስት ግልበጣ በሚደረግባት ቡርኪናፋሶ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡት ፕሬዝዳንት ሮች ማርክ ካቦሬ በሌተናል ኮሎኔል ፖል ሄንሪ ሳንዳጎ ከስልጣናቸው መነሳታቸው ይታወሳል።
መንግስት የገለበጠው ሳንዳጎ ከስምንት ወራት ቆይታ በኋላ በኢምራሂም ትራወሬ ቡድን በመስከረም 2022 በሃይል መነሳቱም አይዘነጋም።
ትራወሬ ከሳንዳጎም ሆነ ከሌሎች የሀገሪቱ የቀድሞ መሪዎች የተሻለ እንደሚሰራና ምርጫ እንደሚያካሂድ ቢገልጽም የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ፈታኝ ችግሮች አልተቀረፉም።
ከአልቃይዳ እና አይኤስ ጋር ግንኙነነት ያላቸው ቡድኖች በቅርብ አመታት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት የቀጠፉ ጥቃቶችን ፈጽመዋል፤ ከ2 ሚሊየን በላይ ሰዎች (ግማሾቹ ህጻናት) ተፈናቅለዋል።
በአሁኑ ወቅት ከሀገሪቱ ክፍል ግማሽ የሚሆነው ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ መሆኑንም ተንታኞች ያነሳሉ።
እንደ ኒጀራና ማሊ ሁሉ ከምዕራባውያን አጋሮች እና የቀድሞ ቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይ ጋር ግንኙነቷን ያቋረጠችው ኡጋድጉ፥ ምርጫ አካሄዳ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንድታካሂድ በምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ተደጋጋሚ ጥሪ ቢቀርብላትም ወታደራዊው ጁንታ አሻፈረኝ ብሏል።
በምርጫ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ስርአት አሸጋግራለሁ ያለው ትራወሬ ሀገሩን ከኢኮዋስ አባልነት በማስወጣት በሀምሌ ወር ሊካሄድ የነበረውን ምርጫ ለአምስት አመት ማራዘምን መርጧል።
ወታደራዊ መኮንኖች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ፣ የባህላዊና ሃይማኖታዊ ቡድኖች መሪዎችን ያካተተው የሽግግር መንግስት ቡርኪናፋሶን ከገጠማት የጸጥታ ችግር የሚያላቅቅ መፍትሄን አላበጀም በሚል ይወቀሳል።
የትናንቱ የጊዜያዊ ፕሬዝዳንቱ ኢብራሂም ትራወሬ ውሳኔም ወታደራዊ ጁንታው የቀደመ ቃሉን እያጠፈ ስልጣኑን የሚያጠናክር እርምጃ መውሰዱን መቀጠሉን ያሳያል መባሉን ሬውተርስ ዘግቧል።