ሚዲያዎቹ ዓለም አቀፉ ሂውማን ራይትስ ዋች የቡርኪናቤ ጦር 223 ንጹሀንን ገድሏል በሚል የወጣውን ሪፖርት መዘገባቸው ለእገዳ ዳርጓቸዋል ተብሏል
ቡርኪናፋሶ ቢቢሲ እና ቪኦኤን ጨምሮ ከሰባት በላይ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን አገደች።
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ቡርኪናፋሶ ከሰባት በላይ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን አግዳለች።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ሂውማን ራይትስ ዋች የቡርኪና ፋሶ ጦር 50 ህጻናትን ጨምሮ 223 ንጹሀንን ገድሏል ሲል ሪፖርት አውጥቷል።
ይህንን ሪፖርት መነሻ በማድረግም በቡርኪና ፋሶ ያሉ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዋቢ አድርገው ዘገባ የሰሩ ሲሆን የሀገሪቱ መንግስትም እገዳ ጥሎባቸዋል፡፡
በቡርኪና ፋሶ መንግስት እገዳ ከተጣለባቸው ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች መካከልም ቪኦኤ፣ ቢቢሲ፣ ለሞንዴ፣ ዘ ጋርዲያን፣ ዶቸቪሌ፣ ቲቭ5 ሞንዴ ኦስት ፍራንስ፣ ኤፒ እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በቡርኪና ወታደራዊ መንግስት እገዳ የተጣለባቸው ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ ያወጡት መግለጫ የለም፡፡
ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪና ፋሶ የአጋርነት ስምምነት ተፈራረሙ
የቡርኪና ፋሶ መንግስት በሚዲያዎቹ ላይ እገዳ የጣለው የሀገሪቱን ጦር ስም አጠልሽታችኋል በሚል ሲሆን የሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርትንም ውድቅ አድርጓል፡፡
በመፈንቅለ ስልጣን ስልጣን የተቆጣጠረው የወቅቱ የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ መንግስት ከምዕራባዊን ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት በየጊዜው በማቋረጥ ላይ ሲሆን እንደ ዓለም ባንክ እና አይኤምኤፍ ያሉ አበዳሪ ተቋማትም ግንኙነታቸውን አቋርጠዋል፡፡
አፍሪካ ህብረት እና የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ወይም ኢኮዋስ ቡርኪናፋሶን ጨምሮ መፈንቅለ መንግስት ያደረጉት ማሊ እና ኒጀርንም ከአባልነት ሲያግድ ሀገራቱ በምላሹ ከኢኮዋስ አባልነት መውጣታቸውን አስታውቀዋል፡፡