ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪና ፋሶ የአጋርነት ስምምነት ተፈራረሙ
መፈንቅለ መንግስት የፈጸሙ ሶስት የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጥቃትን በጋራ ለመከላከል ተስማምተናል ብለዋል
ስምምነቱ በአንዳቸው ላይ የተፈጸመው ጥቃት በሁሉም ሀገራት ላይ እንደተፈጸመ የሚያስቆጥር ነው
ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪና ፋሶ የወታደራዊ አጋርነት ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ምዕራብ አፍሪካዎቹ ኒጀር፣ ቡርኪና ፋሶ እና ማሊ ስልጣን በሀይል የተቆጣጠሩ ወታደራዊ መንግስት የመሰረቱ ሀገራት ናቸው፡፡
ሀገራቱ ከአፍሪካ ህብረት እና ከምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ወይም ኢኮዋስ የታገዱ ሲሆን ስልጣን ወደ ሲቪል አስተዳደድር እንዲመልሱም ተጠይቀዋል፡፡
በያዝነው ክረምት መፈንቅለ መንግስት የተፈጸመባቸው ኒጀር እና ጋቦን ደግሞ የብዙዎችን ትኩረት የሳቡ ሀገራት ናቸው፡፡
የጋቦን ጉዳይ የተረሳ ቢመስልም የኒጀር ጉዳይ ግን የምዕራባዊያን ሀያላን ሀገራት ፍጥጫ የታየባት ሀገር ስትሆን በተለይም ፈረንሳይ የሀይል አማራጮችን ልትጠቀም እንደምትችል ተሰግቷል፡፡
የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ወይም ኢኮዋስ ስልጣን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ቡድን ስልጣኑን ለቀድሞው ፕሬዝዳንት ባዙም ካላስረከበ የሀይል አማራጭ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡
ከማሊና ቡርኪና ፋሶ የተባረረችው ፈረንሳይ ሌላ አፍሪካዊ ሀገር ፍለጋ ላይ መሆኗን ገለጸች
ከዚህ በፊት በተመሳሳይ በሀይል ስልጣን የተቆጣጠሩት የማሊ እና ቡርኪና ፋሶ መሪዎች ለኒጀር ወታደራዊ ቡድን አለን ብለዋል፡፡
ሀገራቱ የሶስትዮሽ ወታደራዊ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን አንዳቸው ለአንዳቸው ጥበቃ ለማድረግ መስማማታቸውን አስታውቀዋል፡፡
የማሊ ወታደራዊ ፕሬዝዳንት ኮለኔል አስሚ ጎይታ ስለ ስምምነቱ እንዳሉት ህዝባችንን ከጥቃት መከላከል የሚያስችል የጋራ ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርመናል ብለዋል፡፡
የሳህል ሀገራት ህብረት የተሰኘው ይህ ስምምነት የሶስቱ ሀገራት ወታደራዊ መሪዎች በማሊ እና ቡርኪናፋሶ አዋሳኝ ስፍራ ላይ ተገናኝተው መፈራረማቸውን ቮኦኤ ዘግቧል፡፡