አሜሪካ ቡርኪና ፋሶን ከአጎአ ንግድ ትስስር መርሀ-ግብር ተጠቃሚነት አገደች
የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር የአጎአን መስፈርት ማሟላት ባለመቻሏ ነው ከመርሀ-ግብሩ የታገደችው
የሀገሪቱ ወታደራዊ መንግስት በሁለት ዓመት ውስጥ ወደ ዲሞክራሲ ለመመለስ ባለፈው ሀምሌ ወር ተስማምቷል
አሜሪካ ቡርኪና ፋሶ "ኢ-ህገመንግስታዊ የመንግስት ለውጥ" አድርጋለች በሚል አጎአ ከተሰኘውና ለአፍሪካ ከቀረጥ ነፃ የንግድ ስራን ከሚፈቅደው መርሀ-ግብር ማስወጣቷን አስታውቃለች።
በፈረንጆቹ 2022 በቡርኪና ፋሶ ሁለት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ተካሂዷል። የቀድሞዎቹም ሆነ የአሁኑ ወታደራዊ መሪዎች ጸጥታን ለማጠናከር ጥረት ቢያደርጉም፤ ነገር ግን የእስላማዊ ጥቃቶች ቀጥለዋል ነው የተባለው።
ሀገሪቱን የተቆጣጠረው ወታደራዊ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ለአሜሪካ ውሳኔ ምላሽ ሲሰጥ ወደ ዲሞክራሲ የሚመለስበት የጊዜ ሰሌዳ አልተቀየረም በማለት የቀድሞ አቋሙን ደግሟል።
ቡርኪና ፋሶ በ24 ወራት ውስጥ ወደ ህገ-መንግስታዊ አስተዳደር ለመመለስ ከምዕራብ አፍሪካ አህጉራዊ ቡድን (ኢኮዋስ) ጋር በሀምሌ ወር ተስማምታለች።
የአሜሪካ አፍሪካ እድገትና እድል ህግ (አጉዋ) ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት የተወሰኑ የብቃት መስፈርቶችን ካሟሉ የንግድና ኢንቨስትመንት መሰናክሎችን በማስወገድ ከቀረጥ ነጻ ምርታቸውን እንዲያስገቡ ያደርጋል።
የአሜሪካ የንግድ ወኪል ጽ/ቤት ቡርኪና ፋሶ የአጎዋ መስፈርትን ማሟላት ተስኗታል ብሏል። የንግድ መርሀ-ግብሩን ወደነበረበት ለመመለስ የሚያስችል "ግልጽ መለኪያዎች" ለሀገሪቱ እንደሚሰጧት ገልጿል።
ከመስፈርቶቹ አንዱ ብዝሀነት ያለው ፖለቲካ ሀገራት መመስረት ወይም መሻሻሎችን ማሳየት አለባቸው።
ከአልቃይዳ እና እስላማዊ መንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች የደህንነት ስጋት የሆኑባት ቡርኪና ፋሶ፤ ይህም በአፍሪካ ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውሶች ያለባት ሀገር አድርጓታል።