ከአላማጣ አዲስ አበባ ሲጓዝ በነበረ አውቶብስ ላይ በደረሰ ጥቃት የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 30 ሰዎች ቆሰሉ
በህዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪ ላይ 'ሸኔ' በተባለ ታጣቂ ቡድን በደረሰ ጥቃት ሹፌርና ረዳት ተገደሉ
ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፈታናና አስጊ ሆኗል
ሀሙስ ሚያዚያ 19፤ 2015 ዓ.ም. ከአላማጣ አዲስ አበባ 45 መንገደኞችን አሳፍሮ የነበረው "የኛ ባስ" በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን በታጣቂዎች በተሰነዘረበት ጥቃት የሰዎች ህይወት አልፏል፡፡
መንገደኞች ለአል ዐይን እንደተናገሩት በመተሀራና በወለንጭቲ ከተሞች መሀል ባለ ስፍራ 'ሸኔ' ብለው የጠሩት ታጣቂ ባደረሰው ጥቃት የአውቶብሱ ሹፌርና ረዳት ተገድለዋል፡፡ እዝራ የተባለ በህይወት የተረፈ መንገደኛ "የውትድርና መለያና ሲቪል የለበሱ ታጣቂዎች" መኪናው እየተጓዘ እያለ የተኩስ እሩምታ መክፈታቸውን ተናግሯል፡፡
ሹፌሩና ረዳቱ ወዲያህ ህይወታቸው እንዳለፈ የተናገረው እዝራ፤ አብዛኛው መንገደኛ በተለይ ደግሞ ሴቶች መቁሰላቸውን ገልጿል፡፡
የጥቃቱን ቅጽበት ሲገልጽ "መኪናው እሄደ ታጣቂዎች ተኩስ ከፈቱ፤ መኪናው አለመገልበጡ እግዚሐብሄር ትረፉ ሲለን ነው" ይላል፡፡
"ሹፌሩና ረዳቱ በእርግጠኝነት እንደሞቱ አይቻቸዋለሁ፡፡ ጭንቅላታቸውን ተመተው ወድቀው ሞተዋል ያልናቸው ሁለት ሰዎችም ነበሩ፡፡ ሌሎቹ እግራቸው፤ እጃቸው የቆሰሉ ናቸው፡፡ አብዛኞቹም የቆሰሉት፤ የተመቱት ሴቶች ነበሩ" ብሏል፡፡
ሹፌሩና ረዳቱ መገደላቸውን ለአል ዐይን ያረጋገጠው የኛ ባስ፤ በጥቃቱ 30 የሚሆኑ መንገደኞች መቁሰላቸውንም ተናግሯል፡፡
የባሱ የስምሪት ክፍል ኃላፊ ስማቸው አቤልነህ፤ ሁሙስ ዕለት 11 ሰዓት አካባቢ በመተሀራና በወለንጭቲ ከተሞች መሀል "ኦነግ ሸኔ" በተባሉ ታጣቂዎች ተኩስ መከፈቱን ተናግረዋል፡፡
ከመንገደኞቹ ውስጥ ወደ አዲስ አበባ እየተመለሱ የነበሩ ሲቪል የለበሱ የመከላከያ ሰራዊት አባላትም ይገኙበታል ብለዋል፡፡
ከ30 በላይ ጥይት አውቶብሱና መንገደኞች ላይ መተኮሱን የገለጹት ኃላፊው፤ ጥቃት አድራሾቹ ወዲያውኑ መሰወራቸውንም ተናግረዋል፡፡
ጥቃቱ መከላከያ ከነበረበት የፍተሸ ጣቢያ (ኬላ) በግምት አንድ ኪ.ሜ ርቀት ላይ እንደነበር የስምሪት ክፍል ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
30ኛ የወንበር ቁጥር ላይ እንደነበር የሚናገረውና ከጥቃቱ የተረፈው እዝራ ተኩሱ በተከፈተ በ10 እስከ 15 ደቂቃ ባለው ጊዜ ውስጥ በጣት የሚቆጠሩ መከላከያ ሰራዊት አባላት ስፍራው ላይ መድረሳቸውን ተናግሯል፡፡
መንገደኛው በድንጋጤ እግሬ አውጭኝ ማለቱንም የአይን እማኙ ገልጿል፡፡
ቁስለኞች ወደ አዳማ ሆስፒታል መወሰዳቸው የተነገረ ሲሆን፤ ጉዳት ያልደረሰባቸው መንገደኞች አዳማ አድረው በማግስቱ ወደ አዲስ አበባ አቅንተዋል ተብሏል፡፡
ሁለት መንገደኞች የገቡበት አልታወቀምም ተብሏል፡፡ ለዚህም በድንጋጤ ወደ ጫካ ገብተው ሊሆን እንደሚችል የስምሪት ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
የማቾች ቀብር ቅዳሜና እሁድ በትውልድ አካባቢያቸው መፈጸሙን የኛ ባስ አስታውቋል፡፡
አል ዐይን የአካባቢውን አስተዳደር ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡
በትራንስፖርት ከጊዜ ወደ ጊዜ ለመንቀሳቀስ ፈተና እየሆነ ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም ጥቃት የማይደርስባቸው "ልዩ ባስ" እየተባሉ የሚጠሩት እንደ የኛ ባስ ያሉት ተሽከርካሪዎች እንደ የትኛውም የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ጥቃት እየደረሰባቸው ነው፡፡
የኛ ባስ በተለይም ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ ባሉ መስመሮች በነጻነት "ደህንነት ተጠብቆ" መስራት አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል ብሏል፡፡
አል ዐይን አማርኛ ጥቃቱን ማረጋገጥ አልቻለም።
ነገርግን በመተሀራ መስመር በመንገደኞችና በአሽከርካሪዎች ላይ በታጣቂዎች ጥቃት ሲደርስ አዲስ አይደለም፡፡
ከጥቃቶቹ ጀርባ ስሙ የሚነሳው "ኦነግ ሸኔ" ወይም "ሸኔ" ቡድን ባለፈው ሳምንት በታንዛኒያ ከመንግስት ጋር ለድርድር ተቀምጧል፡፡
የፌደራል መንግስት ሸኔን ወይም ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እያለ የሚጠራውን ቡድን የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ በሚጥል ተግባር ተንቀሳቅሷል በሚል ነበር ከህወሓት ጋር በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ ያደረገው።
በህወሓት እና በፌደራል መንግስት መካከል ለሁለት አመት የቆየው ግጭት በኘሪቶሪያ በተፈረመው የዘላቂ ተኩስ አቁም ስምምነት ሊቆም ችሏል።
በትግራይም በፌደራል መንግስቱ እውቅና ያለው ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት ተመስርቷል።