“ከላይ የመጣ ትእዛዝ ነው” በሚል ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ በአውሮፕላን መጓዝ መከልከላቸውን መንገደኞች ገለጹ
ክልከላው የህክምና ወረቀት ያላቸው ሰዎች፣ ሽማግሌዎች እና የደርሶ መልስ ቲኬት የያዙትን መንገደኞች አይመለከትም
በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለ19 ወራት አቋርጦት የነበረውን በረራ መጀመሩ ይታወሳል
በመንግስት እና ህወሓት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ላላፉት ሁለት ዓመታት ገደማ ተቋርጦ የነበረውና ከአዲስ አባባ ወደ ትግራይ የሚደረገው የአየር በረራ በቅርቡ ታሕሳስ 19 ቀን 2015 ዓ.ም መጀመሩ የሚታወስ ነው፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አባባ ወደ መቀሌ እንዲሁ አዲስ አበባ ወደ ሽረ መንገደኞችን ጭኖ መደበኛውን አገልግሎት ሲሰጥ ሰንብቷል፡፡
የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩ የተፈራረሙት አካላት ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት ቢሆንም፤ ከታህሳስ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ወዲህ እየተሰማ ያለው የመንገደኞች መስተጓጎል ሁኔታ ግን አሳሳቢ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡
በተለይም ካለፉት ቀናት ጀምሮ ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ በሚመጡ መንገደኞች በኩል ቅሬታ እንዳለ አል-ዐይን አማርኛ ከመንገደኞች ለመረዳት ችሏል፡፡
ሰሞኑን ከመቀሌ አዲስ አበባ ለመምጣት ትኬት ቆርጠው በመቀሌው አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ የተገኙት አብርሃም እና ሃይለ የተባሉ የትግራይ ተወላጅ መንገደኞች ፤ በኤርፖርቱ ባሉ የጸጥታ አካላት መሄድ እንደማይችሉ እንደተነገራቸውና በሁኔታው ቅር መሰኘታቸውን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
“ወደ አዲስ አበባ እንዳንሄድ የተከለከልነው በአውሮፕላን ማረፊያው ውስጥ ባሉ የጸጥታ አካላት (የፌዴራል ፖሊስ አባላት) ነው”፤ እየሆነ ያለው ነገር ፍጹም ያልጠበቅነው ነውም ብለዋል፡፡
ክልከላው በተለይም ከ16 እስከ 64 ባለው የእድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎችን ማዕከል ያደረገ መሆኑ የተናገሩት መንገደኞቹ ፤ ለምን እንደተከለከሉ ሲጠይቁ “ከላይ የመጣ ትእዛዝ ነው” ከሚል ምላሽ ውጭ አሳማኝ ምክንያት ማግኘት እንዳልቻሉም ገልጸዋል፡፡
ባጋጠማቸው የጉዞ መስተጓጎል ምክንያት ከብዙ ነገር መሰናከላቸውና ይህም በሰላም ስምምነቱ ያለን ተስፋ ጥያቄ ውስጥ እንደሆነም ጭምር ተናግረዋል መንገደኞቹ፡፡
ይሁን እንጅ ክልከላው የህክምና ወረቀት ያላቸው ሰዎች፣ ልጆች የያዙ፣ሽማግሌዎች እንዲሁም የደርሶ መልስ ቲኬት የያዙትን መንገደኞች እንደማያካትት ተገልጿል፡፡
የደርሶ መልስ ትኬት ቆርጣ እሁድ እለት ከመቀሌ አዲስ አበባ የመጣችው ሌላዋ የትግራይ ተወላጅ ራሄል ከትግራይ በሚመጡ መንገደኞች ላይ ክልከላ እንደሚደረግ ገልጻ፤ በመቀሌ ካለው በተጨማሪ መንገደኞች አዲስ አበባ ሲደርሱ የሚደረገው ቁጥጥር እጅግ ጥብቅ መሆኑ ተናግራለች፡፡
“አዲስ አበባ ስንደርስ ተለይተን ነው የወረድነው፤ አንደኛ ፎቅ ኢሚግሬሽን ሄደን ሬጅስተር አደረግን፤ የምናርፍበት ቦታ፣ ክፍለ ከተማ፣ ቀበሌ ፣ ስልክ ቁጥራችን ተመዘገበ … ስንወጣ ደግሞ ሻንጣችን እንደገና ተፈትሾ ነው የወጣነው” ስትል ራሄል ተናግራለች ፡፡
ስለጉዳዩ አል-ዐይን አማርኛ ያናገራቸው የአየር መንገዱ ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ክፍል ባልደረባ፤ መንገደኞች እድሜ ተለይተው በአውሮፕላን እንዳይጓዙ ተከልክለዋል የሚለው መረጃ እንዳለ ገልጸው “ጉዳዩ ከአየር መንገድ ጋር የሚያያዝ እንዳልሆነ” ተናግረዋል፡፡
ድምጺ ወያነ ቴሌቪዥን ባሰራጨው ዘገባ ደግሞ ክልከላውን በተመለከተ የትግራይ ባለስልጣናት የሚያውቁት ነገር የለም ብሏል፡፡
ባለስልጣናነቱ “ስለ ክልከላው የምናውቀው ነገር የለም፤ ከፌደራል መንግስት ጋር እንነጋገርበታለን” የሚል ምላሽ መስጠታቸውንም በዘገባው ተመላክቷል፡፡
አንድ ስማቸው አንዲጠቀስ ያልፈለጉ እና ለህወሓት አመራሮች ቅርብ የሆኑ ግለሰበብ ክልከላው ከደህንነት ጉዳዮች ጋር የተያያዘና በፌዴራልም ሆነ በህወሓት ባለስልጣናት እውቅና ሊደረግ የሚችል እንደሆነ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
“በስምምነቱ መሰረት ታጣቂዎች ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንዲመሰሉ መጀመሪያ ተሃድሶ መግባት አለባቸው፤ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ግን ተሃድሶ ሳይገቡ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች እንዳሉ ይገመታል፤ እነዚህ ታጣቂዎች ተሃድሶ ሳይወስዱ በትግራም ሆነ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚጓዙ ከሆነ ለሁለቱም አካላትም ሆነ ለሀገሪቱ ጥሩ አይሆንም” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ግለሰቡ ክልከላው ነገሮች እንኪስተካከሉ ለተወሰነ ጊዜ ሊቆይ የሚችል ነው የሚል ግምት እንዳለቸውም አስቀምጠዋል፡፡