ቶ ሽመልስ አብዲሳ መንግስት የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል
የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በክልሉ ታጥቆ ለሚብቀሳቀሰው የኦነግ ሸኔ ቡድን የሰላም እና የእርቅ ጥሪ አቀረቡ።
ጨፌ ኦሮሚያ በዛሬው እለት መደበኛ ስብሰባውን ማድረግ የጀመረ ሲሆን፣ የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የክልሉ መንግስት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
በዚህም አቶ ሽመልስ፣ "ሰላም ለሁሉም ነገር መሰረት ነው፣ ሰላም በሌለበት ስለ ልማት ማሰብ አይቻልም" ያሉ ሲሆን፣ የኦሮሚያ ክልል መንግስት የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ርእሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ በንግግራቸው፣ "በዚህ በተከበረው ጨፌው ፊት በክልላችን ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ማለትም ኦነግ ሸኔ በእርቅ ወደ ሰላማዊ መንገድ ተመልሶ እንዲገባ በክብር ጥሪ አቀርባለሁ" ብለዋል።
አቶ ሽመልስ አክለውም መንግስት ለሰላም ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ኦነግ ሸኔ እና መሰል የጥፋት ሃይሎች ትክክለኛውን መንገድ እንዲይዙ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን እስከ ህይወት መሰዋእትነት እየከፈሉ ላሉ የጸጥታ አካላትም ምስጋናቸውን ያቀረቡት ርእሰ መስተዳደሩ፣ ለክልሉ ሰላም የሰሩት ስራ ሁሌም በታሪክ ስዘከር ይኖራል ብለዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2013 ግንቦት ወር ላይ በኦሮሚያ ክልል ታጥቆ የሚንምቀሳቀሰውን "ኦነግ ሸኔ" ቡድንን በሽብርተኝትነት መፈረጁ ይታወሳል።
በተለምዶ “ሸኔ” ተብሎ የሚጠራውና በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰዉ ቡድን በርካቶችን ህይወት እንዲጠፋ፣ እንዲፈናቀሉ እና ንብረት እንዲያወድም ከማደረግ በዘለለ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ማጥቃቱንም መንግስት በወቅቱ ገልጸዋል።
“ሸኔ” በ2013 ዓ.ም ብቻ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ 463 ሰዎች ላይ አደጋ ማድረሱ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህ ጥቃት እየተባባ መምጣቱም ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
ቡድኑ ባሳለፍነው ጥር ወር በምስራቅ ወለጋ በፈጸመው ጥቃት ከ50 በላይ ንጹሃን ዜጎችን መግደሉንም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርት አመላክቷል።