የመንግስትና እና ኦነግ ሸኔ ድርድር በታንዛኒያ ተጀመረ
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) እንዳስታወቀው፥ ድርድሩ በታንዛኒያ ከፊል ራስ ገዟ ዛንዚባር ነው እየተካሄደ የሚገኘው
ኢጋድ በድርድሩ ከስምምነት ላይ እንደሚደረስ ተስፋ አለኝ ብሏል
በኢፌዴሪ መንግስት እና በኦነግ ሸኔ መካከል የሚደረገው ድርድር በዛሬው እለት በታንዛኒያ መጀመሩ ታውቋል።
ድርድሩ በታንዛኒያ ከፊል ራስ ገዟ ዛንዚባር መጀመሩን ነው የኢጋድ ቃል አቀባይ መናገራቸውን ጠቅሶ ሬውተርስ የዘገበው።
“በታንዛኒያ እየተካሄደ ያለው ንግግር ወደ ስምምነት ያደርሳል ብለን እንጠብቃለን” ብለዋል የኢጋድ ቃል አቀባይ ኑር ሞሃመድ ሼክ።
ቃልአቀባዩ በድርድሩ እስካሁን ስለተነሱ ነጥቦች ያሉት ነገር የለም።
የፌደራል መንግስቱም ሆነ ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የሚለውና መንግስት ደግሞ ‹ ኦነግ ሸኔ › ሲል የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ድርድሩ ስለመጀመሩ ቢያረጋግጡም ዝርዝር መረጃን አልሰጡም።
በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪው ሬድዋን ሁሴን የድርድር ቡድኑንን እየመሩ እንደሚገኙ የዘገበው ሬውተርስ፥ በኦነግ ሸኔ በኩል እየተሳተፉ የሚገኙትን ወገኖች አልጠቀሰም።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሁለት ቀናት በፊት ከኦነግ ሸኔ ጋር ዛሬ ድርድሩ እንደሚጀምር ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ይህን ድርድር የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ አብዝቶ ይፈልገዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በተለይ “የወለጋ ህዝብ እፎይ ማለት እንዲችል” ሁሉም ወገን የበኩሉን እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውም አይዘነጋም።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2013 ግንቦት ወር ላይ በኦሮሚያ ክልል ታጥቆ የሚንቀሳቀሰውን "ኦነግ ሸኔ" ቡድን በሽብርተኝትነት መፈረጁ የሚታወስ ነው።
በተለምዶ “ሸኔ” ተብሎ የሚጠራውና በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው ቡድን በርካቶችን ህይወት እንዲጠፋ፣ እንዲፈናቀሉ እና ንብረት እንዲያወድም ከማደረግ በዘለለ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ማጥቃቱንም መንግስት በወቅቱ ገልጿል።
“ሸኔ” በ2013 ዓ.ም ብቻ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ 463 ሰዎች ላይ አደጋ ማድረሱ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህ ጥቃት እየተባባሰ መምጣቱም ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በተከታታይ ባወጣቸው መግለጫዎችም በቡድኑ ምክንያት በኦሮሚያ ክልል የዜጎች ደህንነት የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን ማመላከቱ ይታወቃል።
ኦነግ ሸኔ በጥር ወር 2015 በምስራቅ ወለጋ በፈጸመው ጥቃት ከ50 በላይ ንጹሃን ዜጎችን መግደላቸውን ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርት ማሳወቁም የሚታወስ ነው።