"በቀል ከቱልካረም" - በእስራኤል አውቶብሶች ከተገጠሙ ፈንጂዎች ላይ የተጻፈ መልዕክት
በቴል አቪቭ ደቡባዊ ክፍል ሶስት አውቶብሶች የሽብር ጥቃት እንደሆነ በተጠረጠረ ጥቃት ተቃጥለዋል

ፍንዳታውን ተከትሎ በእስራኤል ሁሉም የአውቶብስ እና ባቡር ትራንስፖርት በጊዜያዊነት ተቋርጧል
በእስራኤል መዲና ቴል አቪቭ ደቡባዊ ክፍል ባት ያም በተባለ ስፍራ ሶስት አውቶብሶች ተቃጥለዋል።
አውቶብሶቹ ፈንጂ ተጠምዶባቸው የሽብር ጥቃት ሳይፈጸምባቸው እንዳልቀረ ፖሊስ አስታውቋል።
በማህበራዊ ሚዲያዎች የወጡ ምስሎች በማቆሚያ ስፍራ የነበረ አውቶብስ በእሳት ተያይዞ ሲወድም ያሳዩ ሲሆን፥ ፖሊስ እስካሁን በሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት ሪፖርት አልተደረገም ብሏል።
በሁለት አውቶብሶች ላይ የተገጠሙ ፈንጂዎች ሳይፈነዱ መገኘታቸውን የእስራኤል ፖሊስ ቃል አቀባይ አርዬህ ዶሮን ለቻናል 12 ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
"ሽብርተኞቹ የፈንጂዎቹን የመፈንጃ ጊዜ በተሳሳተ ስአት ላይ ካደረጉት ምናልባት እድለኛ ልንሆን እንችላለን" ያሉት ቃል አቀባዩ በቴል አቪቭ ሌሎች የተጠመዱ ፈንጂዎች ካሉ በሚል የሚካሄደው አሰሳ መቀጠሉን አብራርተዋል።
ፖሊስ ህብረተሰቡ አካባቢውን በንቃት እንዲከታተልና ራሱን እንዲጠብቅም አሳስቧል።
የእስራኤል የትራንስፖርት ሚኒስትር ሚሪ ሬጌቭ ሌሎች የተጠመዱ ፈንጂዎች መኖራቸውን ለማረጋገጥ ሁሉም የአውቶብስ እና ባቡር ትራንስፖርት እንዲቋረጥ ማዘዛቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ጥቃቱን የፈጸሙትን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረቱ መቀጠሉም ተመላክቷል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን 5 ኪሎግራም በሚመዝነውና ሳይፈነዳ ተጠምዶ በተገኘው ፈንጂ ላይ "በቀል ከቱልካረም" የሚል ጽሁፍ እንዳለው ዘግበዋል። "ቱልካረም" የእስራኤል ጦር በሃይል በተያዘችው ዌስትባንክ የጀመረውን "የጸረ ሽብር ዘመቻ" የሚያመላክት ነው ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የእስራኤል ጦር በዌስትባንክ "ዋነኛ የሽብር ማዕከላት" ላይ የተጀመረው ዘመቻ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማዘዛቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል።
በእስራኤል ከተሞች ሌሎች ጥቃቶች እንዳይፈጸሙም ፖሊስና የደህንነት ተቋማት ዝግጁነታቸውን እንዲያሳድጉም ማሳሰባቸውን ነው የተጠቀሰው።
የአውቶብስ ፍንዳታውን ተከትሎ በሞሮኮ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ሚሪ ሬጌቭ ጉብኝታቸውን አቋርጠው ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱ ተዘግቧል።