ሃማስ የአራት እስራኤላውያን ታጋቾች አስከሬንን ለቀይ መስቀል አስረከበ
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ "ዛሬ ለእስራኤላውያን ልብ የሚሰብር የሀዘን ቀን ነው" ብለዋል

የፍልስጤሙ ቡድን ስድስት ታጋቾችን የፊታችን ቅዳሜ እንደሚለቅ አስታውቋል
ሃማስ በጋዛ ታግተው የቆዩ አራት እስራኤላውያን ታጋቾች አስከሬንን ለአለም ቀይ መስቀል ማህበር አስረከበ።
የሶስት የ"ቢባስ ቤተሰብ" አባላት እና የ83 አመቱ ጡረተኛ ጋዜጠኛ አዴድ ሊፍሺትዝ አስከሬን ከካን ዩኒስ ወደ እስራኤል በቀይ መስቀይ ተሽከርካሪዎች እየተጓዘ ነው።
ሽሪ ቢባስ እና በሃማስ ታጣቂዎች በጥቅትምት 7 2023 ሲያዙ የዘጠኝ ወር እና አራት አመት እድሜ የነበራቸው ህጻናት ልጆቿ (ክፊር እና ኤሪያል) የእስራኤላውያን የትግል ምልክት ሆነው ቆይተዋል።
የሃማስ ታጣቂዎች "የቢባስ ቤተሰብ"ን አግተው ሲወስዱ የሚያሳይ ምስል መለቀቁም እስራኤላውያንን ማስቆጣቱን አሶሼትድ ፕረስ አስታውሷል።
የህጻናቱ አባት ያርደን ቢባስ በሌላ ስፍራ በሃማስ ታግቶ በቅርቡ በተደረሰው የታጋቾች እና እስረኞች ልውውጥ ተለቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ "ዛሬ ለእስራኤላውያን ልብ የሚሰብር የሀዘን ቀን ነው" ብለዋል።
ባለፉት ሳምንታት ታጋቾችን በደስታ ሲቀበሉ የነበሩት እስራኤላውያን ዛሬ በከባድ የሀዘን ድባብ ውስጥ ናቸው።
ሃማስ አራቱን ታጋቾች የተገደሉት በእስራኤል የአየር ጥቃት መሆኑን መግለጹና እስራኤል የ"ቢባስ ቤተሰብ" ከተገደሉ "ከባድ ችግር ይፈጠራል" ስትል መዛቷ አይዘነጋም።
የሃማስ መሪ ካህሊል አል ሃያ ዛሬ አስከሬናቸው ወደ እስራኤል ከሚላኩት ውስጥ ሶስቱ የ"ቢባስ ቤተሰብ" አባላት መሆናቸውን ያረጋገጡ ሲሆን፥ ቡድኑ የፊታችን ቅዳሜ ስድስት በህይወት ያሉ ታጋቾችን እንደሚለቅ አስታውቀዋል።
እስራኤልና ሃማስ በጥር ወር በደረሱት የተኩስ አቁምና የታጋቾችና እስረኞች ልውውጥ ስምምነት መሰረት ሃማስ በመጀመሪያው ምዕራፍ 33 ታጋቾችን ለመልቀቅ ተስማምቷል። እስራኤል የስምንት ታጋቾች ህይወት ማለፉን ማረጋገጧን ተከትሎ አሃዙ ወደ 25 ዝቅ ብሏል።
ሃማስ በስድስት ዙሮች 24 ታጋቾችን የለቀቀ ሲሆን እስራኤል ደግሞ 1099 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ፈታለች።
በሁለተኛው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ዙሪያ በኳታር ዶሃ በዚህ ሳምንት ድርድር ይጀመራል ቢባልም ሁለቱም ወገኖች እርስ በርስ እየተካሰሱ ተጓቷል።
የሃማስ ከፍተኛ አመራር ታሄር አል ኑኑ ሃማስ ሁሉንም ቀሪ ታጋቾች በሁለተኛው ምዕራፍ በአንድ ቀን ለመልቀቅ ዝግጁ መሆኑን ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል። አሁን በጋዛ ምን ያህል ታጋቾች እንዳሉ ባይገልጹም እስራኤል ግን ከቀሪዎቹ 70 ታጋቾች የ34ቱ ህይወት ማለፉን መግለጿ የሚታወስ ነው።