
በጥር ወር አጋማሽ በተደረሰው የተኩስ አቁምና የእስረኞች-ታጋቾች ልውውጥ ስምምነት 1100 የሚጠጉ ፍልስጤማውያን እስረኞች ተፈተዋል
ከጥር 19 2025 ጀምሮ ተግባራዊ በሆነው የጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት ሃማስ በስድስት ዙሮች 24 ታጋቾችን ለእስራኤል አስረክቧል።
እስራኤልም የእድሜ ልክ እና ረጅም አመታት እስር የተፈረደባቸውን 1099 ፍልስጤማውያን እስረኞች ፈታለች።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ በሁለቱ ተፋላሚዎች የርስ በርስ ክስ ሊደናቀፍ እንደሚችል ቢገመትም ሃማስ ትናንት ሶስት ታጋቾችን በመልቀቁ ጋዛ ዳግም ወደ ጦርነት ትገባለች የሚለው ስጋት በርዷል።
እስራኤልም 369 ፍልስጤማውያን እስረኞችን መፍታቷ ውጥረቱን አርግቦታል።
እስራኤል በጥቅምት 2023 በሃማስ ታግተው ወደ ጋዛ ከተወሰዱት 251 ሰዎች በእስረኛ ልውውጥና በሌላ ስምምነት 133ቱን አስለቅቃለች።
የጋዛው ጦርነት በተጀመረ በሳምንታት ውስጥ አሜሪካ፣ ኳታር እና ግብጽ አደራዳሪነት በተደረሰው የአራት ቀናት ተኩስ አቁም 150 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ፈታ 50 ታጋቾችን ማስለቀቋ ይታወሳል።
70 ታጋቾች አሁንም በጋዛ እንደሚገኙ ያስታወቀው የኔታንያሁ አስተዳደር 34ቱ ህይወታቸው እንዳለፈ መግለጹ አይዘነጋም።
ቀሪዎቹን ታጋቾች ለማስለቀቅ በሚያስችለው ሁለተኛው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ዙሪያ ስምምነት ላይ ለመድረስ በቀጣዩ ሳምንት በኳታር መዲና ዶሃ ድርድር እንደሚጀመር ይጠበቃል።