ሩሲያ ባለፈው ሳምንት 196 ኪሎሜትር ስኩዌር ስፋት ያለው የዩክሬን መሬት መያዟ ተገለጸ
የሩሲያ ኃይሎች ወደ ፊት መግፋት፣ ሩሲያ በሰው ኃይል እና በጦር መሳሪያ ያላትን የኃይል የበላይነት የሚያሳይ ነው ተብሏል
የሩሲያ ኃይሎች በፍጥነት እየገፉ ሲሆን ምዕራባውያን ጦርነቱን እንዴት ይቁም በሚለው ጉዳይ ላይ ግራተጋብተዋል
ሩሲያ ባለፈው ሳምንት 196 ኪሎሜትር ስኩዌር ስፋት ያለው የዩክሬን መሬት መያዟ ተገለጸ።
ፈጣን ግስጋሴ እያደረገች ያለችው ሩሲያ ባለፈው ሳምንት ከጥቅምት 20-27 196.1 ስኩዌር ኪሎሜትር ስፋት ያለው የዩክሬን መሬት መያዟን ሮይተርስ የዩክሬንን ኦፕን ሶርስ ካርታ የሚተነትነውን የሩሲያ ሚዲያ ቡድን ኤጄንትስትቮን ጠቅሶ ገልጿል።
2 1/2 አመት ያስቆጠረው የዩክሬን ጦርነት የሩሲያ ኃይሎች እጅግ አደገኛ ወደሚሉት ዙር ገብቷል። የሩሲያ ኃይሎች በፍጥነት እየገፉ ሲሆን ምዕራባውያን ጦርነቱን እንዴት ይቁም በሚለው ጉዳይ ላይ ግራተጋብተዋል።
ምንም እንኳን ዩክሬን የሩሲያን ኩርስ ግዛት የወሰነ ክፍል መያዝ ብትችልም፣ፕሬዝደንት ፑቲን በየካቲት 2022 የላኳቸው የሩሲያ ኃይሎች ከመጋቢት 2022 ወዲህ ባለፈው መስከረም ወር በፍጥነት ወደፊት ገፍተዋል።
"የሩሲያ ኃይሎች ቢያንስ ይህ አመት ከገባ ወዲህ እንዲህ አይነት ፈጣን ሳምንታዊ ግስረጋሴ አድርገው አያውቁም" ሲል በሩሲያውያን "የውጭ ኤጀንት" ተብሎ የሚጠራው ኤጄንትስትቮ በቴሌግራም ቻናሉ መግለጹን ዘገባው ጠቅሷል። ኤጀንትስትቮ እንደገለጸው እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሰው የዩክሬንን 'ዲፕ ስቴት ኦፕን ሶርስ ኢንተለጀንስ' ተንታኞችን መረጃ መሰረት በማድረግ ነው።
ባለፈው ሳምንታት የሩሲያ ኃይሎች በቩሌዳር ከተማ አቅራቢያ 95 ኪሎሜትር ስኩዌር እና በፖክሮቭስክ ከተማ ደግሞ 63 ኪሎሜትር ስኩዌር መሬት ተቆጣጥረዋል። ሁለቱም በምስራቅ ዩክሬን በሚገኘው የዶምባስ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
በዶምባስ ግዛት ያለው የዩክሬን ኃይል ኪቭ ወታደሮችን ወደሩሲያ ኩርስክ ግዛት በመላኳ ምክንያት እና ሩሲያ ወታደሮቿን ከዶምባስ ወደ ኩርስክ ባለመላኳ ምክንያት ደክሟል።
የ1/5 የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት የተቆጣጠሩት የሩሲያ ኃይሎች ወደ ፊት መግፋት፣ ሩሲያ በሰው ኃይል እና በጦር መሳሪያ ያላትን የኃይል የበላይነት የሚያሳይ ነው ተብሏል።
ዩክሬን ምዕራባውያን አጋሮቿ ተጨማሪ የጦር መሳሪያ እንዲያስታጥቋት እና በረጅም ርቀት ሚሳይል ሩሲያ ውስጥ ዘልቃ ጥቃት እንድትፈጽም እንዲፈቅዱላት እየተማጸነች ነው።
ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን በከፊል የያዘቻቸውን አራት የምስራቅ እና የደቡብ ዩክሬን ግዛቶችን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ትፈልጋለች።