ኢራን ለእስራኤል ጥቃት ምላሽ ለመስጠት በእጇ "ያሉትን ሁሉንም መሳሪያዎች" እጠቀማለሁ አለች
ኢራን እስራኤል ያደረሰችባትን ጥቃት ቀላል ነው ብላ ብታጣጥልም፣ ለእስራኤል ጥቃት ምላሽ እንደሚያስፈልገው እየገለጸች ነው
የኢራኑ ጠቅላይ መሪ ካሚኒ የኢራን ባለስልጣናት የኢራንን ኃይል ለእስራኤል ማሳየት አለባቸው ብለዋል
ኢራን ለእስራኤል ጥቃት ምላሽ ለመስጠት በእጇ "ያሉትን ሁሉንም መሳሪያዎች" እጠቀማለሁ አለች።
ቴህራን እስራኤል በዚህ ሳምንት መጨረሻ በኢራን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ለፈጸመችው ጥቃት "ሁሉንም አይነት መሳሪያዎች" ተጠቅማ ምላሽ እንደምትሰጥ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል በጋሂ ተናግረዋል።
ባለፈው ቅዳሜ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በመካከለኛው ምስራቅ አጠቃላይ ጦርነት ያስነሳል ተብሎ የተፈራው ውጥረት እንዳይባባስ ጥሪ ሲያደርጉ፣ ኢራን የእስራኤልን ጥቃት "ውስን ጉዳት" ነው ያደረሰው ሰትል አጣጥላው ነበር።
በጋሂ "ኢራን በጽዮናዊው አገዛዝ ላይ ወሳኝ እና ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት እጇ ላይ ያሉ ሁሉንም መሳሪያዎች ትጠቀማለች" ብለዋል።
በጋሂ እክለውም የኢራን ምላሽ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት ባህሪ ላይ የተመሰረተ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከፈጸመች ከሁለት ቀናት በኋላ ባሰሙት ንግግር የኢራን ባለስልጣናት የኢራንን ኃይል ለእስራኤል ማሳየት እንዳለባቸው መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
እስራኤል የፈጸመችው ጥቃት "መናቅም ሆነ መጋነን የለበትም" ብለዋል ካሚኒ።
የእስራኤል ጦር እንደገለጸው ቅዳሜ ማለዳ የእስራኤል አየር ኃይል በቴህራን አቅራቢያ በሚገኙ የሚሳይል ፋብሪካዎች እና ሌሎች ቦታዎች እንዲሁም በምዕራብ ኢራን በሶስት ዙር ከባድ ጥቃት አድርሷል
እስራኤል በኢራን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ጥቃት የፈጸመችው ኢራን ባለፈው ጥቅምት አንድ በ180 ሚሳይሎች በእስራኤል ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ነው።
ኢራን ባለፈው ጥቅምት አንድ በእስራኤል ላይ በስድስት ወራት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ቀጥተኛ ጥቃት ያደረሰችው፣ የእስራኤልን የሊባኖስ ወረራ እና የሄዝቦላ መሪ ነስረላህን ግድያ ለመበቀል ነበር።
ኢራን እስራኤል ያደረሰችባትን ጥቃት ቀላል ነው ብላ ብታጣጥልም፣ ለእስራኤል ጥቃት ምላሽ እንደሚያስፈልገው እየገለጸች ነው።
የሁለቱ ሀገራት ጥቃት መመላለስ አዙሪት የእስራኤል አጋሯን አሜሪካን እና ኢራንን ወደ ቀጥተኛ ቀጣናዊ ግጭት ሊያስገባቸው ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።