ማሊ መፈንቅለ መንግስት ሊፈጽሙ ነበር ያለቻቸውን 49 የኮቲዲቯር ወታደሮች ማሰሯ ይታወሳል
ኮቲዲቯር፤ በማሊ የታሰሩ 50 ገደማ ወታደሮቿ እንዲፈቱ ጠየቀች፡፡
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ማሊ ባሳለፍነው ሳምንት መፈንቅለ መንግስት ሊፈጽሙ ሲያሴሩ ደርሼባቸዋልሁ በሚል 49 የኮቲዲቯር ወታደሮችን አስራለች፡፡
ወታደሮቿ በባማኮ የታሰሩባት ጎረቤቷ ኮቲዲቯር በበኩሏ ወታደሮቼ በማሊ ከተመድ ጋር በገባሁት ስምምነት ሰላም በማስከበር ላይ ናቸው ብላለች፡፡
በማሊ መንግስት የቀረበውን ክስ ውድቅ ያደረገችው ኮቲዲቯር ከፈረንጆቹ 2019 ጀምሮ በሰላም ማስከበር ስራ የተሰማሩ ወታደሮቿ በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁላት ጠይቃለች፡፡
ቀደም ሲል ተሰማርተው የነበሩ ወታደሮችን ሊተኩ ነበር የተባለላቸው የኮቲዲቯር ወታደሮች ከአቢጃን ወደ ባማኮ በመጓዝ ላይ እያሉ በአውሮፕላን ማረፊያ በማሊ መንግስት ቁጥጥር ስር ውለው ነው ባሳለፍነው እሁድ የታሰሩት፡፡
የማሊ ድርጊት ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጋር ያለባትን የተበላሸ ግንኙነት የባሰ ሊጎዳው ከመቻሉ ባለፈ የሽብርተኞችን ጥቃት እንዳያሰፋ ተሰግቷል፡፡
የማሊ መንግስት በበኩሉ የኮቲዲቯር ወታደሮች ሳያሳውቁ እና ሳያስፈቅዱ ወደ ባማኮ መምጣታቸውን ጠቅሶ በወታደሮቹ ፓስፖርት ላይ የተጠቀሱት መረጃዎች ትክክለኛነት የሚጎድላቸው እና ቅጥረኛ ወታደሮች የመሆናቸው እድል በመስፋቱ ሊያስራቸው እንደቻለ ገልጿል፡፡
የኮቲዲቯር መንግስትም ወታደሮቹ ወደ ማሊ የተላኩት ከተመድ ጋር በተደረገ ውይይት መሰረት መሆኑን ገልጾ ወታደሮቹ ምንም አይ ነት የጦር መሳሪያ አለመታጠቃቸውን እንዲሁም ራሳቸውን የሚከላከሉበት መሳሪያ በሌላ አውሮፕላን መላኩን አስታውቋል፡፡
በተመድ የማሊ ተልዕኮ ቃል አቀባይ የኮቲዲቯር መንግስትን ሀሳብ እንደደገፉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
የማሊ ወታደራዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ኮለኔል አስሚ ጎይታ ከተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጋር በስልክ መወያየታቸውን ገልጸው በሰላም ማስከበር ስም የትኛውም ሀገር የማሊን ሉአላዊነት መጣስ እንደማይችል መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡