የተመድ ዋና ጸሃፊው አንቶኒዮ ጉቶሬዝ ቡርኪናፋሶ፣ ጊኒና ማሊ በፍጥነት ወደ ሲቪል አገዛዝ እንዲመለሱ አሳሰቡ
ሶስቱም ሀገራት ከቅርበ ጊዜያት ወዲህ በመፈንቅለ መንግስት ሲታመሱ የቆዩ ሀገራት ናቸው
የጊኒው ጁንታ ትናንት ባወጣው መግለጫ“ስልጣን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለማሸጋገር ቢያነስ 39 ወራት ያስፈልገኛል” ብሏል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ሃላፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ቡርኪናፋሶ፣ ጊኒ እና ማሊ በፍጥነት ወደ ሲቪል አገዛዝ እንዲመለሱ አሳስበዋል።
በአፍሪካ “የረመዳን የአጋርነት ጉብኝት” ላይ የሚገኙት ጉቴሬዝ፤ ሴኔጋል ዳካር ከፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ጋር በነበራው ቆይታ ሶስቱም ሀገራት በፍጥነት ወደ “ህገ-መንግስታዊ ስርአት” ሊመለሱ ይገባል ማለታቸውን ኤ.ኤፍ.ፒ ዘግቧል።
ሶስቱም ሀገራት ማለትም ቡርኪናፋሶ፣ ጊኒ እና ማሊ በሳህል ቀጠና ካለው የጂሃዲስት ዓመጽ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ሀገራት ቢሆኑም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ፤ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ሲታመሱ የቆዩ ናቸው።
በማሊ በነሃሴ 2020 እና በግንቦት 2021፤ በጊኒ መስከረም 2021 እንዲሁም በቡርኪናፋሶ በጥር 2022 መፈንቅለ መንግስት እንደተካሄደ ይታወሳል።
የሴኔጋሉ ፐሬዚዳንት ማኪ ሳል፤ ሶስቱንም ሀገራት ከአባልነት ያገደው የምዕራብ አፍሪካ ህብረት ኢኮዋስ ሊቀመንበር ናቸው።
የምእራብ አፍሪካው ተቋም ኢኮዋስ በማሊ ላይ በጥር ወር ከፍተኛ ማዕቀብ ቢጥልም፤ የማሊው የታደራዊ ኃይሎች ስብስብ እስካሁን ስልጣን ወደ ሲቪል መመልስ ሳይችል ቀርቷል።
ኢኮዋስ ጊኒ እና ቡርኪናፋሶ ሰልጣንን በፍጥነት ወደ ሲቪል አገዛዝ ማሸጋገር ካልቻሉ "በምክንያታዊ" የጊዜ ገደብ ውስጥ ተመሳሳይ ማዕቀብ ሊጣልባቸው እንደሚችል ማስጠንቀቁ አይዘነጋም።
ነገር ግን የሁለቱም ሀገራት ወታደራዊ መንግስታት፤ ኢኮዋስ ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ አልተቀበሉትም።
የቡርኪና ፋሶው ወታደራዊ ኃይል ቀደም ብሎ ይፋ ያደረጉትን የሶስት አመት የሽግግር ጊዜ ለማሳጠር እቅድ እንደሌለው መግለጹ የሚታወስ ነው።
በተመሳሳይ ኢኮዋስ፤ የጊኒው ወታደራዊ ኃይል ቢያንስ በ16 ወራት ውስጥ ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር ማስረከብ አለበት የሚል የጊዜ ገደብ አስቀምጦ የነበረ ቢሆንም፤ የጊኒው ጁንታ የአኮዋስን ምክረ-ሃሳብ እንደማይተገብር በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል።
የጊኒው ጁንታ በትናንቱ መግለጫው “ስልጣን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለማሸጋገር ቢያነስ 39 ወራት ያስፈልገኛል” ብሏል።