የአውሮፓ ህብረት በማሊ ሲሰጥ የነበረውን ወታደራዊ ስልጠና አቆመ
ህብረቱ፤ “ሰሞኑን በማሊዋ ሙራ የተፈጸመውና 200 ሰዎች የሞቱበት ጥቃት አሳዝኖኛል” ብለዋል
ስልጠናው ቢቆምም በሳህል አካባቢ የሚደረጉ ኦፕሬሽኖች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአውሮፓ ህብረት ገልጿል
የአውሮፓ ህብረት በማሊ ሲሰጥ የነበረውን ወታደራዊ ስልጠና ማቆሙ የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሃላፊ ጆሴፕ ቦሬል አስታወቁ፡፡
ህብረቱ ስልጠናውን ለማቆም ከውሳኔ የደረሰው ሰሞኑን ‘ሙራ' በተባለው የማሊ አካባቢ በደረሰ ጥቃት በርካታ ንጹሃን ዜጎች መሞታቸው ተከትሎ ነው፡፡
እንደ ቦሬል ከሆነ ጥቃቱ የተፈጸመው በማሊ ወታደሮች እና የሩስያ ቅጥረኞች ስብስብ እንደሆነ በሚነገርለት ዋግነር ግሩፕ የተሰኘ በማሊ የሚንቀሳቀስ የታጠቀ ቡዱን ነው፡፡
የዋግነር ቡድን የታጠቀ የሩሲያ የግል ወታደራዊ ድርጅት ኃይል መሆኑ ይታወቃል፡፡
ቦሬል "የዋግነር ቡድን ... በቅርብ ጊዜያት በማሊ ለተገደሉት በአስር የሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ተጠያቂ ነው" ብሏል።
ክስተቱን “እልቂት” በማለት የገለጹት ቦሬል “ከሚያስወቅሱ ክስተቶች ጋር መተባበር አንችልም… ለእንደዚህ ዓይነቶቹ ድርጊቶች ተጠያቂ የሆኑትን ሰዎች ማሰልጠን አንችልም ፤ ስለዚህ ለወታደሮች የምንሰጠው ወታደራዊ ስልጠና እናቆማለን” ሲሉም ተባግሯል ።
በዋግነር ቡዱን እንቅስቀሴ ደስተኛ ያልሆኑት ቦሬል፤ በማሊ ውስጥ የተከሰቱት ለውጦች “በቂ ዋስትናዎች እንዳልነበሩ እንድናይ አስገድዶናል” ሲሉም ተደምጧል፡፡
የአውሮፓ ህብረቱ ቦሬል በማሊ የሚንቀሳቀሰውን ዋግነር ቡዱን “ንጹሃንን በመግደልና በጣልቃ ገብነት” ቢፈርጁትም፤ ሩሲያ በበኩሏ በማሊ ያሉት የሩሲያ ወታደራዊ መኮንኖች አውሮፓውያን እንደሚሉት ሳይሆን የወታደራዊ ሳይንስ መምህራን ናቸው ብላለች፡፡
ቦሬል፤ ስልጠናው ቢቆምም በሳህል አከባቢ የሚደረጉ ኦፕሬሽች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
"የሳህል ቀጠና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፤በሳህል የምንቆርጠው ተስፋ የለም ፤ ስለዚህም ለቀጠናው ሰላም በበለጠ እንደምንሰራ ቃል መግባት እንፈልጋለን"ም ብለዋል ቦሬል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ሚኒስትሮች፤ የምዕራብ አፍሪካ አህጉራዊ ቡድን ኢኮዋስ ከማሊ ጁንታ ጋር "ተቀባይነት ያለው ምርጫ" እንዲካሄድ ከስምምነት ላይ እንደሚደርስ ያላቸውን ተስፋ መወያየታቸውንም ጠቁመዋል።
ፈረንሳይ በበኩሏ ባለፈው ወር ብቻ ሙራ በተባለው የማሊ ስፍራ፤ በማሊ ወታደሮችና በዋግነር ቡዱን ተፈጽሟል የተባለውንና ለ200 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን ጥቃት እጅጉን ያሳስበኛል ብላለች፡፡
ሂውማን ራይትስ ዎች፤ የማሊ ወታደሮች እና የውጪ ተዋጊዎች ከመጋቢት 27 እስከ 31 ባለው ጊዜ ውስጥ 300 ንፁሃን ዜጎችን በሙራ መግደላቸው ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።
ፓሪስ፤ ባለፈው አመት ስልጣኑን ከተቆጣጠረው የሀገሪቱ ገዢ መንግስት ጋር ያለው ግንኙነት በመቋረጡ እና የፈረንሳይ አምባሳደር ከባማኮ መውጣታቸውን ተከትሎ፤ በማሊ የነበሩ ወታደሮቿ በየካቲት ወር ማስወጣቷ ይታወሳል፡፡
ፈረንሳይ እንደፈረንጆቹ ጥር 2013; ብዙ ሰሜናዊ ማሊ የተቆጣጠሩትን እስላማዊ ጽንፈኞችን ለመውጋት በሚል በአውሮፓ ህብረት አማካኝነት በሰሜናዊ ማሊ ወታደራዊ ስምሪት ማካሄዷ ይታወቃል፡፡