የዓለማችን በእድሜ ትልቁ ውሻ 31ኛ ዓመት የልደት በዓሉን አከበረ
ለውሻው ረጅም እድሜ የሚኖርበት ረጋ ያለ ሰላማዊ አካባቢ አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሏል
የእድሜ ባለጸጋው ውሻ በፖርቱጋል መንግስት በተፈቀደ የቤት እንስሳት የመረጃ ቋት እድሜው ተረጋግጧል
የጊነስ የዓለም ክብረ ወሰን የዓለማችን አንጋፋ ውሻ 31ኛ ዓመት ልደቱን ማክበሩን ተናግሯል።
ቦቢ የተባለው ውሻው ፖርቹጋላዊ ዝርያ ያለው ሲሆን ልደቱን ሙሉ ህይወቱን በኖረበት በፖርቹጋል ኮንኬይሮስ መንደር አክብሯል።
ከ100 በላይ ሰዎች “ባህላዊ” በተባለው የልደት ድግስ መገኘታቸውን የቦቢ ባለቤት ሊዮን ኮስታ ተናግረዋል።
በልደት ድግሱ ቦቢ በዳንስ እንቅስቃሴው ተሳትፏል።
ሊዮኔል ኮስታ 18 ዓመት የኖረችውን የቦቢ እናት ጊራን ጨምሮ ከዚህ ቀደም ብዙ ያረጁ ውሾች እንደነበሯቸው ገልጸዋል።
ሆኖም ኮስታ ከውሾቹ መካከል አንዳቸውም የ30 ዓመት እድሜ እንደሚደርሱ አስቤ አላውቅም ብሏል።
ኮስታ “እንደዚህ ያሉ ሁኔታዎችን እንደ መደበኛ ህይወት እናያለን። ግን ቦቢ ታይቶ የማይታወቅ ነው” ብለዋል።
ለቦቢ ረጅም እድሜ ትልቅ አስተዋጽኦ ካደረጉት ነገሮች አንዱ የሚኖርበት "ረጋ ያለ፤ ሰላማዊ አካባቢ" ነው ሲሉ ኮስታ ተናግረዋል።
ቦቢ በህይወቱ በሙሉ በኮስታ ቤት ዙሪያ ባሉ ደኖች ውስጥ በነጻነት ሲዞር ቆይቷል።
በሰንሰለት ታስሮ አያውቅም የተባለው ቦቢ፤ "በጣም ተግባቢ" እና በሌሎች ብዙ እንስሳት ተከቦ ያደረገ ነው ተብሏል።
ቦቢ አሁን በእድሜው ምክንያት መራመድ ስለከበደው በጓሮው ውስጥ ቤት መዋልን ይመርጣል።
ቦቢ በፈረንጆቹ 1992 በተመዘገበበት በሌሪያ ማዘጋጃ ቤት የእንስሳት ህክምና አገልግሎት የልደት ቀኑ ተረጋግጧል።
እድሜው በፖርቱጋል መንግስት በተፈቀደ የቤት እንስሳት የመረጃ ቋትም ተረጋግጧል።