የዘንድሮውና 33ኛው አህጉራዊ ውድድር በካሜሩን ይካሄዳል
ኢትዮጵያ የፊታችን ሰኔ በካሜሩን ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ አለፈች።
በካሜሩን በሚካሄደው የዘንደሮው የአፍሪካ ዋንጫ 24 ሀገራት የሚሳተፉ ሲሆን እስካሁን ኢትዮጵያን ጨምሮ 19 ሀገራት ማጣሪያውን አልፈዋል።
የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን በካሜሩን ለሚዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን አረጋግጧል፡፡
ዋልያዎቹ ከኮትዲቯር ጋር ያደረጉት ጨዋታ በኮትዲቯር 3 ለ 1 መሪነት በመካሔድ ላይ እያለ ከ80ኛው ደቂቃ በኋላ የመሀል ዳኛው ተጎድቶ መውጣቱን ተከትሎ ተቋርጧል፡፡
ረዳት ዳኛው ኮትዲቯራዊ መሆናቸውን ተከትሎ ጨዋታውን ሊያስቀጥሉ የማይችሉ መሆኑን ለተጋጣሚዎቹ አምበሎች በመግለጽ ጨዋታው እንዲቋረጥ አድርገዋል፡፡
ይህ ኢትዮጵያ ከነ ሽንፈቷ ጨዋታውን እንዲታጠናቅቅ ቢያስገድድም ማዳጋስካር ከ ኒጀር ዜሮ አቻ መለያየቷን ተከትሎ ለአህጉር አቀፉ ውድድር ማለፏ ተረጋግጧል፡፡
በዚህም ሱዳንን ተከትላ ለውድድሩ ያለፈች ሁለተኛዋ ምስራቅ አፍሪካዊ ሃገር ሆናለች፡፡
ይህ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ ከ8 ዓመታት በኋላ የሆነ ነው፡፡
ዋልያዎቹ ከአሁን ቀደም በሰውነት ቢሻው እየሰለጠኑ ለ31ኛ የአፍሪካ ዋንጫ አልፋ እንደነበር ይታወሳል ምንም እንኳን በቶሎ ከውድድሩ ውጭ ብትሆንም፡፡
ይህን የዋሊያዎቹን ድል ተከትሎ በርካቶች ደስታቸውን በየአደባባዩ በየጎዳናው እየገለጹ ነው፡፡
ሱዳን ደቡብ አፍሪካን በገጠመችበት የማጣሪያ ጨዋታ 2 ለ 0 በማሸነፍ ከምስራቅ አፍሪካ ቀድማ ያለፈች ሀገር መሆን ችላለች፡፡
ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የተመለሰቸው ሱዳን ለመጨረሻ ጊዜ የተሳተፈችው በ2012 የውድድር ዓመት ሲሆን ለሩብ ፍፃሜ ደርሳ ነበር።
እስካሁን በተደረጉ የማጣሪያ ጨዋታዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ ሱዳን፣ ሞሮኮ፣ ናይጀሪያ፣ ኮቲዲቯር፣ ካሜሩን፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ግብጽ፣ ኮሞሮስ፣ ማሊ፣ አልጀሪያ፣ ጋቦን፣ ሴኔጋል፣ ዚምባብዌ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ጋምቢያ፣ ጋና፣ ጊኒ እና ቱኒዚያ ማለፋቸውን የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በድረገጹ አስታውቋል።
ውድድሩ በካሜሩን አምስት ከተሞች ከሰኔ 18 እስከ ሐምሌ 18 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚካሄድ ሀገሪቱ ዝግጅቷን እንዳጠናቀቀች አስታውቃለች።
ማዳጋስካር፣ አንጎላ፣ ቦትስዋና፣ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኢስዋትኒ፣ ኬንያ፣ ሌሴቶ፣ ሊቢያ፣ ናሚቢያ፣ ኒጀር፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛንያ እና ዛምቢያ ከዘንደሮው ውድድር ውጭ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
ጅቡቲ፣ ላይቤሪያ፣ ሲሸልስ እና ሞሪሺየስ በቅድመ ማጣሪያ ውድድር ላይ የተሰናበቱ አገራት ናቸው።
ሶማሊያ እና ኤርትራ በማጣሪያው ውድድር ሳይሳተፉ ሲቀሩ ቻድ ደግሞ በውድድሩ እንዳትሳተፍ ታግዳለች።
የአፍሪካ ዋንጫን ግብጽ ለ7 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ አገር ስትሆን ካሜሩን 5 ጊዜ ጋና 4 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚዎቹ አገራት ናቸው።
በ2019 በግብጽ በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ አልጀሪያ ከሴኔጋል ለፍጻሜ ደርሰው አልጀሪያ ዋንጫ ማንሳቷ ይታወሳል።