ሁሉም ነገር ለወንዶች ቅድሚያበሚሰጥበት ወቅት የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ውጤታማ መሆኑ ከዚህም በላይ መሄድ አንደሚቻል ያሳያል- ሎዛ አበራ
በኢትዮጰያ ከሚወደዱ ስፖርቶች መካከል እግር ኳስ ዋነኛው ሲሆን የወንዶች እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን ከተመሰረተ 84 ዓመት ሲሆን የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ከተመሰረተ ግን ገና 22 ዓመቱ ነው።
አልአይን አማርኛ በሴቶች እግር ኳስ ዙሪያ ከብሄራዊ ቡድኑ እና ከንግድ ባንክ ሴት እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው እና ከብሄራዊ ቡድኑ እንዲሁም ከንግድ ባንክ ተጫዋቿ ሎዛ አበራ ጋር ቃለመጠይቅ አድርጓል፡፡
ለሴቶች እግር ኳስ የተሰጠው ትኩረት፣ የሴቶች ብሄራዊ እግር ኳስ ከወንዶች የተሻለ ስለሆነበት ሚስጥር፣ ስለ ስት እግር ኳስ ተጫዋቾች ፈተና፣ ስለ ቀጣይ እቅዶች፣ እና ሌሎች ጉዳዮች በቃለመጠይቁ የተነሱ ሃሳቦች ነበሩ፡፡
አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው እንዳለው አሁን ላይ አንድ ሴት እግር ኳስ ተጫዋች 100 ሺህ እና ከዚያ በላይ ብር እየተከፈላት ነው፣ የታሰበውን ያክልም ባይሆን የሴቶች እግር ኳስ ቀስ በቀስ እያደገ እና ውጤታማ እየሆነ መሆኑን ተናግሯል።
በኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ እንዲያድግ ከተፈለገ ሁሉም ክለቦች ከወንዶች እኩል የሆነ ትኩረት ሊሰጡ የገባል የሚለው አሰልጣኝ ብርሃኑ በፕሪሚየር ሊጉ የሚሳተፉ ሁሉም ክለቦች የሴት እግር ኳስ ክለብ እንዲያቋቁሙ አሳስቧል።
አሰልጣኝ ብርሃኑ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (ካፍ) መስራቿ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያሟላ አንድም ስታዲየም አለመኖሩ እንደሚያሳፍረው ተናግሯል፡፡
ስታዲየሞቻችን የሙዚቃ ድግስ እና ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄጃ ብቻ ሆነው መቅረት የለባቸውም የሚለው አሰልጣኝ ብርሃኑ እገዳው እንዳይቀጥል የሚጠበቅባቸውን መሰረተ ልማት በአፋጣኝ ማሟላት ስፈልጋል ብሏል፡፡
ከእኛ ያነሰ ህዝብ እና ኢኮኖሚ ያላቸው አፍሪካዊያን ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች እንዳላቸው የሚናገረው አሰልጣኝ ብርሀኑ እኛ በካፍ የታገድነው የስታዲየሞቻችንን ውስጣዊ ክፍል በሚገባ እንኳን ማጽዳት ባለመቻላችን ነው ብሏል፡፡
የብሄራዊ ቡድኑ እንዲሁም ከንግድ ባንክ ተጫዋቿ ሎዛ አበራ በበኩሏ ከዚህ በፊት የነበሩ ሴት እግር ኳስ የብራዊ ቡድን እና የክለብ ተጫዋቾች ብዙ ዋጋ ከፍለዋል ብላለች።
መጫወቻ ሜዳ፣ ትራንስፖር፣የላብ መተኪያ እነ ሌሎች መሰረታዊ ነገሮች ሳይሟሉ ለብሄራዊ ቡድን እና ለክለቦች ሲጫወቱ ነበር የምትለው ሎዛ አሁን ብዙ ነገሮች እየተቀየሩ መሆኑን ተናግራለች።
አሁን ላይ የሴቶች ብሄራዊ ቡድን እና ክለቦች ከወንዶች በተሻለ መንገድ ውጤታማ እየሆነ ነው ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? በሚል ላነሳንላት ጥያቄም “ሴቶች በአንጻራዊነት ሃላፊነትን ይወጣሉ፣በልምምድ አይቀልዱም ፣ጉዳት አለብኝ እና ሌሎች ምክንያቶችን አይደረድሩም ውጤታማ የሆንነው ለዚህ ነው” ስትል ሎዛ ተናግራለች።
ይህ አንጻራዊ ዉጤት የተገኘው ሁሉም ነገር ለወንዶች ቅድሚያበሚሰጥበት ወቅት መሆኑ ደግሞ ከዚህ በተሻለ መንገድ ለሴቶች የመጫወት እድል፣ማበረታቻዎች እና ሌሎች ድጋፎች ቢሰጥ ደግሞ የበለጠ ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም ሎዛ ገልጻለች።
ሴቶች አሁን ላይ ወደ እግር ኳስ መጫወቻ ሜዳዎች በነጻነት መምጣት ጀምረዋል፣ወላጆችም እግር ኳስ መጫወት የሚፈልጉ ልጆቻቸውን እየለቀቁ ነው የምትለው ሎዛ በዛው ልክ ግን ውድድሮች እና ተጫዋቾችን የሚያቅፉ ክለቦች እያደጉ አለመሆኑ ያሳስባል ብላለች።
በአሰልጣኝ አስራት አባተ ይመራ የነበረው እና እኔ በአምበልነት የመራሁት ከ20 ዓመት በታች የሴቶች እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን በጋና መሸነፋችን እና ለዓለም ዋንጫ አለማለፋችን ሁሌ እንደሚቆጫት ሎዛ አንስታለች።
ከዚህ በተጨማሪም በአፍሪካ የክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ ለማለፍ ከጫፍ ደርሰን በኬንያው ክለብ ቪጋ መሸነፋችን ሌላኛው ቁጭቴ ነውም ብላለች ሎዛ አበራ።
እግር ኳስ ተጫዋች ባልሆን የህክምና ሙያ ባለቤት መሆኔ የማይቀር ነው የምትለው ሎዛ አሁን የደረሰችበት የእግር ኳስ ደረጃ ልጅ ሆኜ ስታልመው የነበረ መሆኑንም ገልጻለች።
ወደ እግር ኳስ ተጫዋችነት የሚመጡ ወጣት ሴቶች ብዙ ፈተናዎች እንደሚጠብቋቸው አውቀው ዝግጁ ሆነው እንዲመጡም ሎዛ አሳስባለች።
ለአብነትም ከቤተሰብ ርቆ የመምጣት፣ የመጫወት እድል ማጣት፣ ብቸኝነት እና ሌሎች ፈተናዎች ሊያጋጥሟቸው እንደሚችሉ ተናግራለች።
በመሆኑም ወጣት ሴቶች ስኬታማ እግር ኳስ ተጫዋች ለመሆኑ ከጎጂ ነገሮች ራስን ማራቅ፣ አዋዋልን መምረጥ፣ ተስፋ አለመቁረጥ ፣ አላማን በሚገባ መረዳት እና ሌሎች ጽናት የሚጠይቁ ፈተናዎችን መቋቋም እንዳለባቸው አሳስባለች።
የሴቶች እግር ኳስ ከዚህ የበለጠ እንዲያድግ ሴት አሰልጣኞች፣ዳኞች እና ሌሎች እግር ኳሱ የሚጠይቃቸው ባለሙያዎች የግድ መጨመር አለበትም ብላለች ሎዛ አበራ።