የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም መታገዱን ተከትሎ ኢትዮጵያና ጋና በደቡብ አፍሪካ ሊጫወቱ ነው
የባሕር ዳር ስታዲየም በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መታገዱ ይታወሳል
ጨዋታው በደቡብ አፍሪካ ኦርላዶ ስታዲየም የሚካሄደው ኢትዮጵያ መምረጧን ተከትሎ ነው
የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ከጋና ብሔራዊ ቡድን ጋር ያለበትን ጨዋታ በደቡብ አፍሪካ ኦርላዶ ስታዲየም እንዲያካሂድ ኢትዮጵያ መምረጧን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
ኢትዮጵያ ይህንን ምርጫ የመረጠችው የባሕር ዳር ስታዲየም በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ከታገደ በኋላ ነው።
የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በካፍ መታገዱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታውን ከሀገር ውጭ ለማድረግ መገደዱን ፌዴሬሽኑ ገልጿል።
ፌዴሬሽኑ በአማራጭነት ኬንያ፣ዚምቧቤን እና ደቡብ አፍሪካን መምረጡን የገለጸ ሲሆን፤ ሶስቱም ሀገራት ጨዋታውን ለማስተናገድ ፈቃደኝነታቸውን መግለጻቸውን አስታውቋል።
ከዚህ በመነሳትም የዚምቧቤ ስታዲየም፤ የዚምቧቤን እና የኢትዮጵያን ጨዋታ ብቻ እንዲያስተናግድ በገደብ የተፈቀደለት በመሆኑ ሌላ ጨዋታ ማካሄድ እንደማይችል ካፍ በማረጋገጡ አማራጭ ሳትሆን ቀርቷል ነው የተባለው።
ኬንያም በተመሳሳይ ፈቃደኝነቷን የገለጸች ቢሆንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ዚምባቡዌ ለመጨረሻ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታው ማቅናቱ ስለማይቀር፤ በአንድ የአውሮፕላን ጉዞ እና መጠነኛ ወጪ ጨዋታውን በደቡብ አፍሪካ ለማድረግ እንደተወሰነ ነው ይፋ የተደረገው።
በመሆኑም ጨዋታው ፊፋ በሚያስቀምጠው ቀን በደቡብ አፍሪካ ኦርላዶ ስታዲየም ለማድረግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከደቡብ አፍሪካው አቻው ጋር ተስማምቷል ተብሏል።