ፕሬዝዳንቱ ይህንን ጉብኝት ሲያደርጉ ስልጣን ከጨበጡ ወዲህ ሁለተኛ የውጭ ጉዞዋቸው መሆኑ ነው
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ከዛሬ ሃምሌ 3 ቀን 2022 ጀምሮ የሶስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ተርኪዬ ማቅናታቸውን የአንካራ ባለስልጣናት አስታወቁ።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ወደ ተርኪዬ የሚያቀኑት ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ባደረጉላቸው ግብዣ መሰረት መሆኑን አናዶሉ ዘግቧል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት መሪዎቹ፤ የሀገራቱ ሁለትዮሽ ግንኙነት እና ትብብርን ለማጎልበት በሚያስችሉ ጉዳዮችና እርምጃዎች ዙሪያ ጥልቅ ውይይት እንደሚያደርጉ የተርኪዬ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
መግለጫው "ሁለቱ መሪዎች በአህጉራዊ እና አለምአቀፋዊ ለውጦች ላይ ሀሳብ ይለዋወጣሉም" ብሏል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ይህንን ጉብኝት ሲያደርጉ በትረ ስልጣን ከጨበጡ ወዲህ ሁለተኛ የውጭ ጉዞዋቸው መሆኑ ነው፡፡
ሀሰን ሼክ መሀሙድ ከሁለት ሳምንታት በፊት በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ይፋዊ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡
ፕሬዝዳንቱ ወደ አቡዳቢ ያቀኑት የአረብ ኢምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ባደረጉላቸው ግብዣ መሰረት እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
የጉብኝቱ ዋና ዓላማ “የሁለቱን ወንድማማች ሀገራት ግንኙነት ለማሻሻል እና ለማጠናከር” እንደነበርም ይታወሳል፡፡
በቅርቡ የሶማሊያ ፕሬዝዳንትነት በትረ ስልጣን የተቆጣጠሩት ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ “ሰላም የሰፈነባት እና ከዓለም ጋር ሰላም ያላት ሀገር ለማድረግ እሰራለሁ” ሲሉ ቃል መግባታቸው አይዘነጋም፡፡
ለዚህም ፕሬዝዳንቱ ፤ ሶማሊያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር መልካም የሚባል ወዳጅነትና ዝምድና እንዲኖራት በዲፕሎማሲው መስክ በርካታ ስራዎች መስራት እንደሚጠበቅባቸው ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
የአሁኑ የፕሬዝዳንቱ የተርኪዬ ጉቡኝትም ታዲያ የዚሁ አንድ አካል ነው ተብሏል።