ካፍ የአፍሪካ ሀገራት የ2022 የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ውድድር ጊዜን አራዘመ
የማጣሪያ ውድድሮቹ በመስከረም፣ ጥቅምት ፣ ህዳር እና የካቲት ወር ላይ እንዲካሄዱ ውሳኔ አሳልፏል
የአፍሪካ ሀገራት በኳታር 2022 የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ በ10 ምድቦች ተከፋፍለው ይፋለማሉ
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የአፍሪካ ሀገራት የ2022 የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ውድድር የሚካሄድበትን ጊዜ አራዘመ።
የአፍሪካ ሀገራት የኳታር 2022 የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ውድድሮች ከፊታችን ሰኔ ወር ጀምሮ እንደሚያካሂዱ ከዚህ ቀደም የወጣው መርሃ ግብር ያመላክታሉ።
ሆኖም ግን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ባካሄደው አስቸኳይ ስበስባ ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ ባጋጠሙ ፈተናዎች እንዲሁም ለሁሉም ተሳታፊ ሀገራት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በሚል የውድድር ጊዜውን ለማራዘም ወስኗል።
በዚህም መሰረት ለ2022 የኳታር የዓለም ዋንጫ ፣ የአፍሪካ ሀገራት የማጣሪያ ውድድር በቀጣዩ ዓመት መስከረም፣ ጥቅምት እና ህዳር እንዲሁም የካቲት ወር ላይ እንዲካሄዱ ውሳኔ አስልፏል።
የጨዋታዎቹ ሙሉ መርሃ ግብር ወደፊት የሚገለጽ መሆኑንም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በድረ ገጹ ባወጣው መረጃ አስነብቧል።
የአፍሪካ ሀገራት በኳታር 2022 የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ በ10 ምድቦች ተከፋፍለው የሚወዳደሩ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም በምድብ 7 ከደቡብ አፍሪካ፣ ጋና እና ዚምባቡዌ ጋር የምትጫወት ይሆናል።
ከየምድቡ 1ኛ ሆነው የሚያጠናቅቁ 10 ብሔራዊ ቡድኖች ለሁለት ተከፍለው በሚያደርጉት የጥሎ ማለፍ ውድድር በ2022 የዓለም ዋንጫ አፍሪካን የሚወክሉ ሀገራ እንደሚለዩም ተገልጿል።