“ካፍ በባህርዳር ስታዲየም ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ ወቅቱን ያልጠበቀ ነው”- የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት
ይህን ተከትሎ ዋሊያዎቹ ከጋና ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ በደቡብ አፍሪካ ኦርላንዶ ስታዲየም እንደሚያካሄዱ መገለጹ ይታወሳል
ካፍ በባህር ዳር ስታዲየም ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች እንዳይደረጉ እገዳ መጣሉ ይታወሳል
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ተገምግሞ በቀጣይ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን እንዳያስተናግድ የጣለው እገዳ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑን የአማራ ክልል አስታወቀ፡፡
የክልሉ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት እንዳለው ካፍ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ ወቅቱን ያልጠበቀ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጋና ጋር በቀጣይ የሚያደርገውን ጨዋታ በባህር ዳር ስታዲየም እንደማይደረግ ካፍ በመከልከሉ ጨዋታው በደቡብ አፍሪካ ኦርላንዶ ስታዲየም እንዲካሄድ ኢትዮጵያ መምረጧን ይታወሳል፡፡
ይህ ውሳኔ የመጣው ካፍ የባሕር ዳር ስታዲየም ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ብቁ አይደለም በሚል በማገዱ ሲሆን የአማራ ክልል ግን ይህንን እንደማይቀበለው ገልጿል፡፡
ካፍ ለእገዳው በምክንያትነት ካነሳቸው አስተያየቶች መካከል፤ የተጨዋቾች መልበሻ ክፍል ግብዓቶችን ማሟላት፣ የክብር እንግዶች መቀመጫ ጣራ ስራ፣ የሚድያ ክፍል ማዘጋጀት፣ የተጠባባቂ ተጫዋቾች መቀመጫ፣እንዲሁም የሜዳ ሳር እንዲቀየር የሰጠው አስተያየት አግባብነት የሌላቸው አስተያየቶች ናቸው ብሏል ክልሉ፡፡
በክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ፋሲሊቲ ዳይሬክተር አቶ ባንታምላክ ሙላት የስታድየሙን ጣራ ማልበስ፣ በምሽት ጨዋታወችን ማካሄድ የሚያስችል የመብራት ስራ፣የተመልካቾች መቀመጫ ወንበር እና የስርዓተ ድምፅ ግብዓቶችን ማሟላት ከፍተኛ ወጭ የሚጠይቁና ከክልሉ መንግስት አቅም በላይ በመሆናቸው በክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አማካኝነት ከሚመለከተው አካል ጋር መነጋገር መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡
ካፍ የአፍሪካ ሀገራት የ2022 የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ውድድር ጊዜን አራዘመ
የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ ካሳ፤ የባህርዳር አለም አቀፍ ስታድየም ለዓመታት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን በማስተናገድ ለሀገር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተ በመሆኑ ፋይዳው ሀገራዊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ስታዲየሙ ስታንዳርዱን እንዲያሟላ ካፍ ከሰጣቸው አስተያየቶች መካከል በክልሉ አቅም ሊሸፈኑ የሚችሉትን ለመስራት የአጭር፣ መካከለኛና የረጅም ጊዜ ዕቅድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።