የአንድነት ፓርክን እስካሁን ከ37 ሺ በላይ ሰዎች ጎብኝተዋል ተባለ
በኢትዮጵያ ታላቁ ቤተመንግሥት በ40 ሔክታር መሬት ላይ የተገነባው አንድነት ፓርክ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ፣ ባለፈው መስከረም 29/2012 ዓ.ም. የኢትዮጵያና የተለያዩ ሀገራት መሪዎች በተገኙበት ተመርቆ ከቀጣዩ ቀን ጀምሮ ነው ለህዝብ እይታ ክፍት የሆነው፡፡
ፓርኩ ለህዝብ እይታ ክፍት ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ37 ሺ በላይ ጎብኚዎችን ማስተናገዱን የአንድነት ፓርክ ዋና ዳይሬክተር ታምራት ሀይሌ (ዶ/ር) ለኢቢሲ ገልጸዋል፡፡
ጎብኚዎቹ ከመላው ዓለም የመጡ መሆናቸውንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ፓርኩ በውስጡ ኢትዮጵያኝ በአጭሩ የሚተርኩ የተለያዩ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ተፈጥሯዊ መስህቦችን በአንድነት አጣምሮ የያዘ ነው፡፡
የአንድነት ፓርክ ከሰኞ ውጭ በሳምንቱ ስድስት ቀናት የሀገር ውስጥም ይሁን የውጭ ጎብኚዎችን ያስተናግዳል፡፡
ለፓርኩ ግንባታ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን የገንዘብ ድጋፉ የተገኘው ከዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ መሆኑን ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ምንጭ፡- ኢቢሲ