አሜሪካ “ለመውለድ ብቁ አይደሉም” በሚል ተገደው እንዲመክኑ የተደረጉ ሰዎችን ልትክስ ነው
በርካቶች እንዲመክኑ ከተደረጉባቸው የአሜሪካ ግዛቶች አንዷ ካሊፎርኒያ ናት
“ለመውለድ ብቁ አይደሉም” የተባሉ በርካታ ሰዎች በአሜሪካ ከአስርት ዓመታት በፊት በግድ እንዲመክኑ መደረጉ ይነገራል
ከአሜሪካ ክፍለ ግዛቶች አንዱ የሆነው ካሊፎርኒያ ለመውለድ ብቁ አይደሉም በሚል በግድ እንዲመክኑ ለተደረጉ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ካሳ ሊከፍል ነው፡፡
በነፍስ ወከፍ እስከ 25 ሺ ዶላር ሊደርስ ይችላል የተባለለት የካሳ ክፍያ ከአስርት ዓመታት በፊት በግድ እንዳይወልዱ ለተደረጉ በሺዎች ለሚቆጠሩ የድርጊቱ ሰለባዎች የሚከፈል ነው ተብሏል፡፡
ካሳው እንዲከፈል የግዛቱን ዋና አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውሰምስን ፊርማ ብቻ እንደሚጠብቅም ነው የተነገረው፡፡
ይህ ካሊፎርኒያን በ1930ዎቹ ሲደረግ በነበረው ዘር የመምረጥ ንቅናቄ (American eugenics movement) ሰለባዎች ካሳ ከከፈሉት ከቨርጂኒያ እና ሰሜን ካሮላይና በመቀጠል ለንቅናቄው ሰለባዎች ካሳ የከፈለች ሶስተኛዋ አሜሪካ ግዛት ያደርጋታል፡፡
እንደ አሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ ከሆነ በወቅቱ የነበሩት የንቅናቄው አቀንቃኞች የአዕምሮ ታማሚዎችን፣ አካል ጉዳተኞችን ሌሎች መሰሎችንም ማምከኑ የጠራ የሰው ልጅ ዘርን ለማግኘት ያስችላል የሚል ግምት ነበራቸው፡፡
ይህ በህግ ተደግፎ ሲደረግ የነበረም ነው፤ ምንም እንኳን ህጉ በ1970ዎቹ መጨረሻ ቢሻርም፡፡
ካሳ ክፍያው በእስር ላይ ሳሉ ተገደው እንዲመክኑ የተደረጉ እንስቶችን እንደሚመለከትም ነው የተገለጸው፡፡
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ2005 እስከ 2013 ባሉት አመታት በካሊፎርኒያ 144 ሴቶች እንዲመክኑ መደረጉን የቅርብ ጊዜ የኦዲት ግኝቶች አመልክተዋል፡፡
ከ144ቱ ውስጥ አብዛኞቻቸው ያለ ፍቃዳቸው ወይም ሳያውቁ እንዲመክኑ የተደረጉ ናቸው፡፡
በካሊፎርኒያ በግድ ማምከን የተጀመረው በ1909 ነው፤ ከዋሽንግተን እና ኢንዲያና ግዛቶች በመቀጠል፡፡ ሆኖም የካሊፎርኒያው ብዙዎች የመከኑበት ነው፡፡
ህጉን ከለላ አድርገው በአሜሪካ ምድር ከተፈጸሙት ዘርን የማምከን እርምጃዎች የከፋው ነው በሚባልለት በዚህ እርምጃ በካሊፎርኒያ 20 ሺ ገደማ ሰዎች እንዲመክኑ መደረጉም ይነገራል፡፡
ይህ እስከ 1999 ቀጥሎ ታራሚዎች በግድ እንዲመክኑ ይደረግም ነበረ፡፡ ሆኖም ከ2014 ጀምሮ በህግ እንዲታገድ ተደርጓል፡፡