አሜሪካ ቱርክን ህጻናትን ለውትድርና ከሚመለምሉ ሃገራት ዝርዝር ውስጥ አስገባች
አንካራ ከእንዲህ ዓይነቱ ዝርዝር ውስጥ የገባች የመጀመሪያዋ የኔቶ አባል ሃገር ነች
ቱርክ በሶሪያና በሊቢያ ጦርነቶች በእጅ አዙር የምትደግፋቸው ቡድኖች ህጻናትን ለውትድርና በመመልመል በተደጋጋሚ የሚከሰሱ ናቸው
አሜሪካ ቱርክን ባለፈው ዓመት ህጻናትን ለውትድርና መልምለዋል ካለቻቸው ሃገራት ዝርዝር ውስጥ ከተተች፡፡
ዋሽንግተን የሰሜን አትላንቲክ ጦር (ኔቶ) አባል የሆነችውን አጋሯን ቱርክን ከእንዲህ ዓይነቱ ዝርዝር ስታስገባ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
ይህ መሆኑ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየሻከረ የመጣውን ግንኙነታቸውን የበለጠ እንዳያሻክረው ተሰግቷል፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አንካራ በሶሪያ ለበሽር አል አሳድ ተቃዋሚ ሱልጣን ሙራድ ጦር ተጨባጭ ድጋፎችን ማድረጓን በሪፖርቱ አረጋግጧል፡፡
አንካራ ለረዥም ጊዜ የደገፈችው የሱልጣን ሙራድ ጦር ዋሽንግተን ህጻናትን ለጦርነት ይመለምላል በሚል ቀድማ ፈርጃዋለች፡፡
ይህን የአሜሪካን እርምጃ በተመለከተ ቱርክ እስካሁን የሰጠችው ይፋዊ ምላሽ የለም እንደ ሲ.ኤን.ኤን ዘገባ፡፡
ህጻናቱ በሊቢያ ጭምር መሰማራታቸውንም ነው “ዋሽንግተን ጉዳዩን ለመፍታት ከአንካራ ጋር ትሰራለች” ያሉ አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ባልደረባ ለጋዜጠኞች የገለጹት፡፡
ቱርክ አይ ኤስ አይ ኤስን ለማዋጋት በሚል በሶሪያ ሶስት ያህል ድንበር ዘለል ዘመቻዎችን አድርጋለች፡፡
ዘመቻዎቹ በሶሪያ የሚንቀሳቀሱና በአሜሪካ የሚደገፉ የኩርዲስታን ታጣቂዎችን መውጋትንና የአሳድ መንግስት ተቃዋሚ የሆኑ ታጣቂዎችን መደገፍን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው፡፡
በአንካራ የሚደገፉት ከእነዚህ ታጣቂ ቡድኖች መካከል ደግሞ አንዳንዶቹ በንጹሃን ግድያና በተለያዩ ወንጀሎች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጭምር የሚከሰሱ ናቸው፡፡