አሜሪካ በሊቢያ የሚገኙ የውጭ ጦር አባላትና ቅጥረኞች እንዲወጡ አሳሰበች
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን ጆይ ሁድ ትሪፖሊን ጎብኝተዋል
ዋሽንግተን ጠንካራ ሊቢያን ማየት እንደምትሻና ፖለቲካዊ ሽግግሩን እንደምትደግፍም አስታውቃለች
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን ጆይ ሁድ ትሪፖሊን ጎበኙ፡፡
ጉብኝቱ አሜሪካ ለ“ሊቢያ ሽግግር መንግስት” ያላትን ድጋፍ የሚያመለክት ነው ተብሏል፡፡
ባለስልጣኑ በትሪፖሊ በነበራቸው ቆይታ የሊቢያን ሰላም እውን ለማድረግ አሁንም “እስካሁን በሊቢያ የሚገኙ የውጭ ኃይሎች እና ቅጥረኞች” ሊወጡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ከ2014 ወዲህ ትሪፖሊን የጎበኙት የቅርብ ምስራቅ (Near East) ጉዳዮች ተጠባባቂ ዋና ፀኃፊና ከፍተኛ ባለስልጣኑ ጆይ ሁድ “አሜሪካ ማንኛውንም ዓይነት ወታደራዊ ውጥረት እና የውጭ ጣልቃ ገብነት የውጭ ታጣቂዎች እና የውክልና ጦርነትንም ጭምር ትቃወማለች” በማለትም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ሁድ ሁሉም የሊቢያና የውጭ ኃይሎች ለተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊነት በኃላፊነት እንዲሰሩም ማሳሰቢያ አዘል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሁድ በትሪፖሊ ቆይታቸው ከሊቢያው ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብዱልሀሚድ ድቤባህ ጋር የተወያዩ ሲሆን “የአሜሪካ ዋና ዓላማ ካለ ምንም ጣልቃ ገብነት ሉዓላዊነቷ የተከበረ፣ የተረጋጋችና አንድነት ያላት ብሎም አሸባሪነትን መግታት የምትችል ሊቢያን ማየት ነው” ሲሉ ገልጸውላቸዋል፡፡
ሊቢያ እ.ኤ.አ 2011 ሞዓመር ጋዳፊ ከስልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ መረጋጋት ተስኗት እስካሁን የተለያዩ ተዋናዮች እየፈነጩባት የምትገኝ ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡
የተ.መ.ድ ዋና ጸኃፊ አንቶንዮ ጉቶሬዝ በሊቢያ ስምምነት ቢደረስም አሁንም ያልወጡ የውጭ ኃይሎች እንዳሉ መረጋገጡን ከሶሞኑ መግለፃቸው የሚታወስ ነው፡፡ 20ሺህ የሚሆኑ የሶርያ እና ሱዳን ወታደራዊ ኃይሎች እንደሆኑም ጭምር፡፡