ካሜሩን ስለ አዛውንቱ ፕሬዝዳንቷ የጤና ሁኔታ ማውራትን በህግ ከለከለች
ለረጅም ጊዜ ከህዝብ እይታ ተሰውረው የሰነበቱት የ91 አመቱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ፖል ቢያ የጤና ሁኔታ በዜጎች መነጋገርያ ሆኗል
ፕሬዝዳንቱ በጠና እንደታመሙ የሚናፈሱ ወሪዎች መበራከታቸውን ተከትሎ መንግስት ስለ ፕሬዝዳንቱ የጤና ሁኔታ በየትኛውም ሁኔታ እንዳይወራ በህግ ከልክሏል
ካሜሩን ስለ አዛውንቱ ፕሬዝዳንቷ የጤና ሁኔታ ማውራትን በህግ ከለከለች።
ካሜሩን ለረጀም ጊዜያት ከህዝብ እይታ ተሰውረው ስለቆዩት ፕሬዝዳቷ ፖል ቢያ የጤና ሁኔታ በሀገር ውስጥ እንዳይወራ በህግ አገደች፡፡
የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በፕሬዝዳንቱ የጤና ሁኔታ ዙሪያ የሚናፈሱ ወሬዎች በዜጎች ዘንድ አለመረጋጋት እና ሽብርን እየፈጠሩ ስለሚገኝ በየትኛውም ሁኔታ ስለ ጤና ሁኔታቸው ማውራትም ሆነ መወያየት በህግ ያስቀጣል ብሏል፡፡
ስለፕሬዝዳንቱ የጤንነት ሁኔታ በመገናኛ ብዘሁን መወያየት የብሔራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥል ነው የተባለ ሲሆን ህጉን በሚተላለፉት ላይ ከበድ ያለ ቅጣት እንደሚጣል ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡
በተጨማሪም የፖል ቢያ የጤና ሁኔታ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እና በአሁኑ ወቅት ለይፋዊ የስራ ጉብኝት በሲውዘርላንድ ጄኔቫ እንደሚገኙ ሚንስቴሩ አስታውቋል፡፡
የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትሩ ፖውል አታንጋ የግዛት አስተዳዳሪዎች በግል መገናኛ ብዙሀን እና በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚሰራጩ መሰል መረጃዎች ላይ ክትትል እና ቁጥጥር እንዲያደርጉ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
መንግስት ጉዳዩ በህግ የሚያስቀጣ ተግባር እንደሆነ ቢያሳውቅም ከአፍሪካ ቻይና ጉባኤ በኋላ ለአምስት ሳምንታት ከህዝብ እይታ ውጭ ሆነው የቆዩት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጉዳይ የዜጎች ዋነኛ አጀንዳ ሆኗል፡፡
በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾ ፖል ቢያ በሕይወት ካሉ ማረጋገጫ እንፈልጋለን የሚሉ ጹሁፎች በሰፊው እየተዘዋወሩ እንደሚገኙም ተሰምቷል፡፡
በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች መንግስት በደረቁ ፕሬዝዳንቱ በህይወት አሉ ብቻ እያለ ከሚከራከር ማረጋገጫ በመስጠት ህዝቡን እንዲያረጋጋ ጠይቀዋል፡፡
ካሜሩን ከአንድ አመት በኋላ ምርጫ ለማድረግ እየተዘጋጀች በምተግኝበት በዚህ ወቅት መሰል ሁኔታዎች በሀገሪቱ አለመረጋጋትን እንዳይፈጥሩ ስጋት እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡
በካካዋ ምርቷ የምትታወቀው የማዕከላዊ አፍሪካዊቷ ሀገር ካሜሩን በ1960ዎቹ መጀመርያ ከፈረንሳይ እና እንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች በኋላ ላለፉት 64 አመታት ለሚጠጋ ጊዜ የነበሯት ሁለት ፕሬዝዳንቶች ብቻ ናቸው
የ91 አመቱ ፖል ቢያም በአፍሪካ ለረጅም አመታት ከመሩ እና በህይወት ከሚገኙ መሪዎች በስልጣን ዘመናቸው ርዝመት ሁለተኛው ናቸው፡፡