ተጠቂዎች ላይ ሳይጠጡ የትንፋሽ ለውጥንና መንገዳደግን ጨምሮ ሌሎች የስካር ምልክቶች ይታያሉ
ተመራማሪዎች አንዳንድ ሰዎች ላይ ምንም አይነት አልኮል ሳይጠጡ ስካር ሊያጋጥም እንደሚችል ከሰሞኑ አስታውቀዋል።
እንዲህ አይነቱ እክል “አውቶ ቢርዌሪ ሲንደረም” ይባላል ያሉት ተመራማሪዎቹ፤ ችግሩ እምብዛም ባይታይም አልፎ አልፎ ሊከሰት እንደሚችል አስታውቀዋል።
በአሜሪካ ኒውዮርክ የጉበት ህክምና ኢንስቲትዮት ተመራማሪ የሆኑት ደ/ር ዶጉላስ ዲትሪች፤ እንዲህ አይነቱ ችግር የሚያጋጥመው አንጀታችን በፈንገስ ሲወረር ነው ብለዋል።
ይህም አንጀታችን በፈንገስ ከተወረረ በኋላ በውስጣችን ያለውን ካርቦሃይድሬት እና ስኳርን በማፍላት ወደ አልኮሆል እንዲቀየር በማድረግ ስካሩ እንዲፈጠር እንደሚያደርግ ዶ/ር ዶጉላስ ተናግረዋል።
ደ/ር ዶጉላስ ዲትሪች አክለውም የህክምና ባለሙያዎች እንዲህ አይነት ነገር ሲያጋጥማቸው “አውቶ ቢርዌሪ ሲንደረም” ህክምና ከማድረጋቸው በፊት "ሁልጊዜ ሌሎች መንስኤዎችን መመልከት እና ታማሚው በድብቅ አለመጠጣቱን ማረጋገጥ አለባቸው" ብለዋል።
“አውቶ ቢርዌሪ ሲንደረም” በትክክል አጋጥሞ ያውቃልʔ
ለዚህ ጥያቄ መልሱ አዎ ሲሆን፤ ችግሩ በቅርቡ የተስተዋለውም እድሜዋ 50 ዓመት በሆነች ካናዳዊት ሴት ላይ መሆኑ ተነግሯል።
የካናዳ ሜዲካል አሶሴሽን ጆርናል በቅርቡ ባተመው ጽሁፉ ላይ ምንም አይነት አልኮል ጠጥታ በማታውቅ የ50 ዓመት እድሜ ያላት ሴት ላይ ስካር መከሰቱን አስታውቋል።
በግለሰቧ ላይ ከፍተኛ የሆነ በአልኮል የመመረዝ ምልከቶች የታዩ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ የአፍ ጠረኗ የአልኮል ሽታ መሽተትን ጨምሮ፣ ስትናገር አንደበት የመተሳሰር እና በደሟ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው አልኮል መታየቱም ነው የተገለጸው።
የታካሚዋ የቅርብ ጊዜ የህክምና ታሪክ ላይም በሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ተጠቅታ እንደነበረ እና ለዚህም በርከት ያሉ አንቲ ባዮቲክሶች እንዲሁም በሆዷ ውስጥ ያለ የአሲድ መጠንን ለመቀነስ ህክምናዎችን መውሰዷን ያመለክታል።
በታካሚዋ ላይ በተደረገ የሀክምና ክትትልም “አውቶ ቢርዌሪ ሲንደረም” ተጠቂ መሆኗ መረጋገጡም በጆርናሉ ተመላቷል።
በካናዳ የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ተላላፊ በሽታዎች እና የማይክሮ ባዮሎጂ ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ራሄል ዘዉዴ የጥናቱ መሪ ሲሆኑ፤ “አውቶ ቢርዌሪ ሲንደረም” በታካሚዎችና ቤተሰቦቻቸው ላይ ሰዎች ከፍተኛ የህክምና፣ የህግ፣ የማህበራዊ እና የገንዘብ መዘዞችን ያመጣል ብለዋል።
ስለዚህ ስለዚህ እምብዛም ስለማይታወቀው “አውቶ ቢርዌሪ ሲንደረም” ዙሪያ ለህክምና ማህበረሰቡም ይሁን ለህብረተሰቡ ንዛቤ መፍጠር በህክምና ላይ የሚከሰቱ መዘግየቶችን ያስቀራል ስሊም መክረዋል።