በትራምፕ አስተዳደር ታሪፍ የተጣለባቸው ካናዳ፣ ሜክሲኮና ቻይና ምን ምላሽ ሰጡʔ
ትራምፕ በካናዳና ሜክሲኮ የ25 በመቶ፤ በቻይና ላይ ደግሞ የ10 በመቶ ታሪፍ የሚጥል ትእዛዝ ፈርመዋል

ካናዳና ሜክሲኮ ተመሳሳይ የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በካናዳ፣ ሜክሲኮ እና በቻይና ላይ ታሪፍ የሚጥል ትእዛዝ መፈራረማቸው ይታወቃል።
በፕሬዝዳንት ትራምፕ ትእዛዝ መሰረትም በካናዳና ሜክሲኮ የ25 በመቶ፤ በቻይና ላይ ደግሞ የ10 በመቶ ታሪፍ የሚጣል ይሆናል።
በትራምፕ በተፈረመው ትዕዛዝ መሠረት በካናዳ ፣ በሜክሲኮ እና በቻይና ዕቃዎች ላይ የተጣለው ቀረጥ ከማክሰኞ እኩለ ሌሊት ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።
በካናዳ የኢነርጂ ምርቶች ላይ የሚጣለው የ10 በመቶ ቀረጥ ከየካቲት አጋማሽ ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።
ትራምፕ እነዚህን ታሪፎች ለምን ጣሉ?
ትራምፕ ታሪፉን ለመጣል የአለም አቀፉን የአደጋ ጊዜ ኢኮኖሚ ሃይሎች ህግ (IEEPA) ተጠቅመዋል የተባለ ሲሆን፤ ኢላማ የተደረጉት ሀገራት ህገ ወጥ ስደትን ወይም ወደ አሜሪካ የሚደረጉ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ለማስቆም በቂ ስራ ባለማድረጋቸው ነው ሲሉ ከሰዋል።
ታሪፍ የተጣለባው ሀገራት ምን ምላሽ ሰጡʔ
የትራምፕን የታሪፍ ውሳኔ ተከትሎ ሰለባ የሆኑት ካናዳ፣ ሜክሲኮ እና ቻይና በጽኑ ያወገዙ ሲሆን፤ የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስዱም ዝተዋል።
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ “ትራምፕ ውሳኔ ለዓለም ስጋት ነው” ያሉ ሲሆን፤ በአሜሪካ ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ቀረጥ መጣላቸውን አስታውቀዋል።
ይህም 155 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ባላቸው ምርቶች ላይ ነው የ25 በመቶ ታሪፍ ይፋ ያደረጉት ።
ትሩዶ እንደተናገሩት ካናዳ የምትጥለው ታፍ የአሜሪካ ቢራ እና ወይን እንዲሁም የፍራፍሬ እና የፍራፍሬ ጭማቂዎች ላይ ኢላ ያደረገ ነው።
ልብሶችን፣ የስፖርት ቁሳቁሶችን እና የቤት እቃዎችን ጨምሮ እቃዎችን የካናዳ ታሪፍ ኢላማዎች ናቸው።
የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሺንባም በአሜሪካ ምርቶች ላይ ታሪፍ መጣልን ጨምሮ አጸፋ እርምጃ እንዲወሰድ ትእዛዝ አስተላልፈዋል።
ሜክሲኮ ለተጣለባት ታሪፍ በአይነት ምላሽ ለመስጠት ትገደዳለች ያሉት ፕሬዝዳንት ክላውዲያ፤ "የሜክሲኮን ጥቅም ለመጠበቅ ታሪፍ እና ታሪፍ ነክ ያልሆኑ እርምጃዎችን የሚያካትት፣ እየሰራንበት ያለው አማራጭ እቅድ እንዲተገብር ለኤኮኖሚ ሚኒስትሬ መመሪያ ሰጥቻለሁ ብለዋል።
የቻይና መንግስት በፕሬዝዳንት ትራምፕ የተጣለውን ታሪፍ በጽኑ ያወገዘ ሲሆን፤ ቤጂንግ ትራምፕ የሚያቀርቡትን ቤጂንግ ወደ አሜሪካ የሚፈሰውን ገዳይ የሆነውን ኦፒዮይድን መግታት ዙሪያ እና እየከፋ የንግድ ግጭት እንዳይፈጠር ለውይይት በሯን ከፍት መሆኑን አስታውቃለች።
ቻይና ህጋዊ መብቷን እንዲሁም ጥቅሟን ለማስጠበቅ አጸፋዊ እርምጃ እንደሚኖራትም አሳስባለች።