የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጄስቲን ቱሩዶ ከስልጣናቸው ሊለቁ እንደሚችሉ ተገለጸ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዜጎች ያላቸው ተቀባይነት በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን ተከትሎ ነው ስልጣንቸውን ሊለቁ እንደሚችሉ የተነገረው
በመሪው ከፍተኛ ተቀባይነት ማጣት የተደናገጠው ሊበራል ፓርቲ በመጪው ረቡዕ አስቸኳይ ስብሰባ ለማድረግ ቀጠሮ ይዟል
በዜጎች በከፍተኛ ደረጃ ተቀባይነት ያጡት የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጄስቲን ቱሩዶ ከስልጣናቸው ሊለቁ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡
ሮይተርስ ከአስተዳደሩ ጋር ቅርበት ያላቸውን ምንጮች ጠቅሶ እንደዘገበው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ባይደርሱም ስልጣን ሊለቁ የሚችሉበት እድል ከፍተኛ መሆኑን አስነብቧል፡፡
ትሩዶ ከካናዳ ገዥው ሊበራል ፓርቲ ከዘጠኝ ዓመታት የስልጣን ቆይታ በኋላ ከሀላፊነት መልቀቃቸውን እስከ መጪው ረቡዕ ድረስ እንደሚያሰውቁ ይጠበቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ስልጣን መልቀቃቸው ፓርቲያቸውን ያለ መሪ የሚያስቀር ከመሆኑም በዘለለ ከህዝብ የተሰበሰቡ አስተያየቶች እንደሚያሳዩት በቀጣይ አመት በሚደረገው ምርጫ የሊበራል ፓርቲ በወግ አጥባቂ ፓርቲ ሊሸነፍ የሚችልበት እድል ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የሊበራል ፓርቲ የፓርላማ አባላት ትሩዶ ከስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቁ ድምጾች ከጊዜ ወደጊዜ እየተበራከቱ መምጣታቸውን ተከትሎ በፓርቲያቸው ቀጣይነት ዙሪያ ከነገ በስቲያ ረቡዕ አስቸኳይ ስብሰባ ለማድረግ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡
ለአስር አመት በተጠጋ ጊዜ በስልጣን ላይ የነበሩት ጀስቲን ትሩዶ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው የገቧቸውን ቃሎች አልፈጸሙም በሚል ይተቻሉ፡፡
ከዚህ ባለፈ በሀገሪቱ ሚገኝው የኑሮ ውድነት የመኖሪያ ቤት ኪራይ መናር እና ሌሎችም ችግሮች ዜጎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ከስልጣን መነሳት አጥብቀው እንዲሹ ያደረጓቸው ምክንያቶች ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቱሩዶ ከስልጣን ለመልቀቅ የሚወስኑ ከሆነ ፓርቲያቸው አዲስ መሪ እስኪሾም ፣ አልያም ምርጫ እስከሚደረግ በሀላፊነት እንደሚቆዩ ወይም ወዲያው ከስልጣን እንደሚለቁ የታወቀ ነገር የለም፡፡
ግሎብ ኤንድ ሜል ከምንጮች አገኝሁት ባለው መረጃ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገንዘብ ሚኒስትራቸው ዶሚኒክ ልብላንክ እሳቸውን ተክተው በጊዜዊነት እንዲያስተዳድሩ መመካከራቸውን አስነብቧል፡፡
የወግ አጥባቂ ፓርቲው በበኩሉ ዋናው የምርጫ ጊዜ ሳይጠበቅ አስቸኳይ ምርጫ በማድረግ ተመራጩን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መቋቋም የሚችል የተረጋጋ መንግስት በቶሎ እንዲቋቋም ጫና እያሳደር ይገኛል፡፡