ኔቶ ሩሲያና ቻይና ስልታዊ አጋርነት መፍጠራቸው የህብረቱን እሴትና ጥቅም የሚፈታተን መሆኑን አስጠንቅቋል
ካናዳ በሚቀጥለው ወር ወታደራዊ ወጪዋን እንደምታሳድግ ይጠበቃል።
ነገር ግን ጭማሪው አዳዲስ ስጋቶች ያንዣበበባቸው አጋሮቿ መተማመኛ እንደማይሆንና የሀገሪቱን ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ታማኝነት የበለጠ ሊያዳክም ይችላል ሲሉ የፖሊሲ ተንታኞች ተናግረዋል።
የካናዳ ወታደራዊ ኢንቨስትመንት ውስንነት የሚታወቅ ቢሆንም፤ ሩሲያ ዩክሬን ላይ የጀመረችው ጦርነት የኔቶ ህብረት ላይ ስጋት ፈጥሯል።
ሰፊው የአርክቲክ አካባቢዎችም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የበለጠ ተደራሽ እየሆኑ በመምጣታቸው ስጋቱ ይበልጥ አሳሳቢ ሆኗል።
የኔቶ ዋና ጸሃፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ ባለፈው ነሃሴ የካናዳ አርክቲክን ጎብኝተው ሩሲያና ቻይና ስልታዊ አጋርነት መፍጠራቸው የምዕራቡን ወታደራዊ ህብረት እሴትና ጥቅም የሚፈታተን መሆኑን አስጠንቅቀዋል።
በ2022 ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 1 ነጥብ 29 በመቶ የሆነው የካናዳ የመከላከያ ወጪ በ1990ዎቹ መገባደጃ በኋላ ጭማሪ አላሳየም።
በጀቱ ኔቶ ለአባላቱ ካቀደው ሁለት በመቶ በታች ነው ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
የኔቶ የ2022 አማካይ የመከላከያ ወጪ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 2 ነጥብ 58 በመቶ ነው።
የኔቶ መስራች አባል የሆነችው ካናዳ ከሁለት ሳምንት በኋላ በሊትዌኒያ ከሚካሄደው የኔቶ የመሪዎች ጉባኤ በፊት የመከላከያ ወጪን ለመጨመር ቃል እንደምትገባ ይጠበቃል።
ኔቶ በጉባዔው ሀገሪቱ ተጨማሪ ወጪ እንድትመድብ ግፊት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።