ካናዳ ከጠቅላላ የውጭ ንግዷ ውስጥ 75 በመቶ ምርቶቿን ወደ አሜሪካ የምትልክ ሲሆን ዶናልድ ትራምፕ አዲስ የግብር ጭማሪ አደርጋለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ስጋት አይሏል
ዶናልድ ትራምፕ ካናዳ ወደ አሜሪካ እንድትጠቃለል ጠየቁ፡፡
ሰሜን አሜሪካዋ ካናዳ በተለይም ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን ካሸነፉ በኋላ የፖለቲካ አለመረጋጋት አጋጥሟታል፡፡
ለዜጎቿ የተሻለ አገልግሎት እና ህይወት በመስጠት የምትታወቀው ካናዳ የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር ከሆነችው አሜሪካ ጋር ጎረቤት መሆኗ ለገጠማት የፖለቲካ አለመራጋጋት መነሻ ሆኗል፡፡
ሀገሪቱ ወደ ውጭ ሀገራት ከምትልካቸው ምርቶቿ ውስጥ 75 በመቶውን ወደ ጎረቤቷ አሜሪካ የምትልክ ሲሆን ሁለት ሚሊዮን ዜጎቿ ህይወታቸው በዚህ ንግድ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ካናዳ እና ሜክሲኮ ምርቶቻቸውን በገፍ ወደ አሜሪካ ምርቶች እየላኩ ነው፣ የሚከፍሉት ግብርም ዝቅተኛ ነው በሚል ጭማሪ አደርጋለሁ ሲሉ ዝተዋል፡፡
ይህ የዶናልድ ትራምፕ እቅድ በተለይም ካናዳን በእጅጉ ይጎዳል የተባለ ሲሆን ትራምፕ ቃላቸውን ከተገበሩ የሚለው ሀሳብ የካናዳ ፖለቲከኞችን እና ዜጎችን ስጋት ላይ ጥሏል፡፡
ትራምፕ አክለውም ካናዳዊያን የተባላችሁትን ግብር ካልከፈላችሁ የአሜሪካ 51ኛዋ ግዛት ሆናቸው ተቀላቀሉን ሲሉ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከዚህ በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶን በይፋዊ ስልጣናቸው ከመጥራት ይልቅ ገዢ እያሉ ሲጠሩ ተደምጠዋል፡፡
ከሰሞኑ በተደረገ የህዝብ ፍላጎት ማወቂያ ጥናት መሰረት 13 በመቶ ካናዳዊያን ከሀገርነት ይልቅ የአሜሪካ 51ኛዋ ግዛት ቢሆኑ ይመርጣሉ ተብሏል፡፡
ካናዳ በገጠማት የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር በራሳቸው ፈቃድ ከሃላፊነት መልቀቃቸው ይታወሳል፡፡