ህንድ 41 የካናዳ ዲፕሎማቶች ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አዘዘች
በህንድ 62 ዲፕሎማቶች ያሏት ካናዳ የምትወስደው አጻፋዊ እርምጃ የሀገራቱን ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያሻክረው ይጠበቃል
የህንድና ካናዳ ግንኙነት በሲክ ተገንጣይ ቡድን መሪው ግድያ ምክንያት ሻክሯል
ህንድ 41 የካናዳ ዲፕሎማቶች ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ማዘዟ ተነገረ።
ፋይናንሽያል ታይምስ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ሰዎች ጠቅሶ እንደዘገበው ዲፕሎማቶቹ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከህንድ እንዲወጡ ታዟል።
ካናዳ በህንድ 62 ዲፕሎማቶች ያሏት ሲሆን፥ አጠቃላይ አሀዙን ወደ 21 ዝቅ የሚያደርግ ውሳኔ በኒው ደልሂ በኩል መተላለፉ ነው የተገለጸው።
በዲፕሎማቶቹ መባረር ዙሪያ የህንድም ሆነ የካናዳ የውጭ ጉዳይ መስሪያቤቶች እስካሁን ማብራሪያ አልሰጡም።
የህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱብራህማንያም ጃይሻካር ግን በካናዳ በሚገኙ የህንድ ዲፕሎማቶች ላይ ጫና የመፍጠርና “የማሸማቀቅ” ሙከራ እየተደረገ ነው ማለታቸውን ሬውተርስ በዘገባው አስታውሷል።
ካናዳ የሲክ ተገንጣይ ቡድን መሪው ሃርዴፕ ሲንግ ኒጃር በሰኔ ወር በሀገሪቱ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ በተባለው አካባቢ የተገደለው በህንድ መንግስት ትዕዛዝ መሆኑን የሚያሳይ መረጃ አለኝ ካለች በኋላ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ሻክሯል።
ኒውደልሂ የሽብር ቡድን አድርጋ የፈረጀችው ቡድን መሪ ግድያ ውስጥ እንዳልተሳተፈች በመግለጽ ተቃውሞዋን የካናዳን ዲፕሎማት በማባረር ገልጻለች።
ኦቶዋም የህንድን ከፍተኛ የደህንነት ሹም ማባረሯ የሚታወስ ነው።
ህንድ 41 የካናዳ ዲፕሎማቶችን እስከ ጥቅምት 10 2023 ሀገሬን ለቃችሁ ውጡልኝ ማለቷን ተከትሎም የጀስቲን ትሩዶው መንግስት የሚያሳልፈው አጻፋዊ ውሳኔ ይጠበቃል።
የሲክ ህዝቦች ጥያቄ ለምን ህንድና ካናዳን ያወዛግባል?
በፑንጃብ ግዛት የሚገኙት የሲክ ህዝቦች ነጻ ሀገር የመመስረት ትግል የጀመሩት በፈረንጆቹ 1980 ነው።
የመገንጠል እንቅስቃሴውን ለመግታትም የህንድ ወታደሮች በ1984 ከ400 በላይ የሲክ ማህበረሰብ አባላት ላይ እርምጃ መውሰዳቸውን የሬውተርስ ዘገባ ያወሳል።
በወቅቱ ወታደራዊ እርምጃውን ያዘዙት የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢንድራ ጋንዲም በጥቅምት ወር 1984 ከሲክ ወገን በሆኑ ሁለት ሴት ጠባቂዎቻቸው መገደላቸው ነው የሚነገረው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ “ካሊስታኒስ” እያሉ በሚጠሯቸው የሲክ ህዝቦች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዳቸውን የመብት ተሟጋቾች ይገልጻሉ።
ኒው ደልሂ ባለፈው አመትም የሲክ ህዝቦችን መገንጠል የሚያቀነቅነውን ቡድን መሪ ሃርዴፕ ሲንግ ኒጃር ለጠቆመኝ ጠቅም ያለ ሽልማት እሰጣለሁ ማለቷ የሚታወስ ነው።
ኒጃር እና የሚመሩት ተገንጣይ ቡድንን እንደ ሽብርተኛ የምትቆጥረው ህንድ እንቅስቃሴው የብሄራዊ ደህንነቴ ስጋት ነው በማለት በህግ አግዳዋለች።
ይሁን እንጂ እንቅስቃሴው በሰሜን ህንድ፣ ካናዳ እና ብሪታንያ ድጋፍ እንዳለው ነው የሚነገረው።
በርካታ የሲክ ዲያስፖራዎች በሚገኙባት ካናዳ ነዋሪ የነበሩት ሃርዴፕ ሲንግ ኒጃር የሲክ ወይንም "ካሊስታን"ህዝብ የራሱን ሀገር እንዲያቋቋም ህዝብ ወሳኔ ለማድረግ ቅስቀሳ ላይ እያሉ ተገድለዋል።