ካናዳ ለግለሰቦች የጦር መሳሪያ እንዳይሸጥ ያግዛል የተባለ ሕግ አዘጋጀች
ሕጉ መሳሪያ መግዛትና መሸጥን ወደ ሀገር ማስገባትና ማስተላለፍንም ይከለክላል ተብሏል
በካናዳ በጦር መሳሪያ ምክንያት እየደረሰ ያለው ችግር መቀጠሉ ተገልጿል
ካናዳ፤ የጦር መሳሪያ በግለሰቦች እጅ እንዳገባና እንዳይሸጥ ያደርጋል የተባለ ሕግ ማዘጋጀቷን አስታወቀች፡፡
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ መሳሪያን በግለሰብ ደረጃ እንዳይያዝ የሚያደርግ ብሔራዊ ሕግ አዘጋጅተው ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡ ሕጉ የጦር መሳሪያ እንዳይሸጥ ብቻ ሳይሆን ከሌላ ቦታም ወደ ካናዳ በማምጣት ባለቤት እንዳይሆኑ እንደሚከለክል ተገጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሀገራቸው ይህንን ሕግ ያዘጋጀችው ለግለሰቦች መሳሪያ መሸጥን ሙሉ ለሙሉ ለማስቆም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ጀስቲን ትሩዶ በጦር መሳሪያ ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን ያጡ በርካታ ሰዎች በተገኙበት ነው ሕጉ መዘጋጀቱን ያስታወቁት፡፡
ካናዳ ግለሰቦች የጦር መሳሪያ እንዳይገዙና ባለቤት እንዳይሆኑ እንደሚያግዝ ያሰበችውን ሕግ ለማዘጋጀት መነሻ የሆናት ከሰሞኑ በአሜሪካ በአንድ ትምህርት ቤት አንድ ግለሰብ በከፈተው ተኩስ በርካቶች ለህልፈት መዳረጋቸው ነው ተብሏል፡፡
በተዘጋጀው ሕግ መሰረት ከዚህ በኋላ በካናዳ ግዛት ውስጥ የጦር መሳሪያ መሸጥ፣ መግዛት፣ ከውጭ ማስገባትና ማዘዋወር እንደማይቻል ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ ገልጸዋል፡፡ በሌላ አነጋገር የጦር መሳሪያ ግብይት እገዳ ተጣለበት ወይም ተከለከለ ማለት እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
የተዘጋጀው ሕግ በምክር ቤት መጽደቅ እንዳለበት የተገለጸ ቢሆንም ገዥው የሊብራል ፓርቲ ግን በምክር ቤቱ ያለው መቀመጫ አነስተኛ ነው ተብሏል፡፡ በካናዳ ግለሰቦች በሚይዙት የጦር መሳሪያ ምክንያት በርካቶች እንደሚሞቱ ይገለጻል፡፡ ለአብነትም ሚያዚያ 2020 በደረሰ ጥቃት 23 ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ሲሆን መንግስት በ 1500 አይነት መሳሪያዎች ላይ ዕገዳ አስቀምጦ ነበር፡፡
ምንም እንኳን ዕገዳ ቢቀመጥም በጦር መሳሪያ ምክንያት እየደረሰ ያለው ችግር መቀጠሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡