መንግስት የካፒታል ገበያ በመጪው ዓመት አጋማሽ ወደ ስራ ይገባል አለ
ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ ዳግም የሚጀመረው የካፒታል ገበያ ለአየር ንብረት ፋይናንስ አይን ተጣለበት
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሚቀጥሉት 30 ዓመታት 34 ቢሊዮን ዶላር ከሀገር ውስጥ አሰባስባለሁ ብላለች
የኢትዮጵያ መንግስት በ2015 መጀመሪያ ላይ የጸደቀው የካፒታል ገበያ ቀናት በቀሩት አዲስ ዓመት አጋማሽ ላይ እንደሚጀምር አስታውቋል።
ሀምሌ 29 በጀመረው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የተገኙት የፕላንና ልማት ሚንስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በፈረጆቹ 2024 መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን እንደምትጀምር ተናግረዋል።
ይህም ሀገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና መቋቋም ለምታደርገው የገንዘብ ማሰባሰብ አንደኛው መንገድ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ “የረጅም ዘመን ዝቅተኛ ልቀትና የአየር ንብረት መቋቋሚያ የልማት ሰትራቴጂ” የተባለ የ30 ዓመት እቅድ ይፋ ያደረገች ሲሆን፤ እቅዱ ሀገሪቱ ልማቷን በአየር ንብረት ለውጥ መነጽር የምትመራበትን ፍኖተ ካርታ ነው።
ሀገሪቱ በፓሪስ ስምምነት መሰረት የተደረሰበትን የሙቀትና የልቀት መጠን ላይ ለመድረስ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሚቀጥሉት 30 ዓመታት 170 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋት ተነግሯል።
ከእዚህም ውስጥ 20 በመቶው ማለትም 34 ቢዮን ዶላር (1.9 ትሪሊዮን ብር ገደማ) ከሀገር ውስጥ የገንዘብ አማራጮች እንደሚሰበሰብ ሚንስትሯ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ሀገሪቱ ለአየር ንብረት መከላከልና መቋቋሚ የምትመድበው የሀገር ውስጥ ገንዘብ በአመዛኙ ከመንግስት (ከፐብሊክ ፋይናስ) የሚመነጭ ነው።
በመንግስት የሚመደበው ገንዘብ ችግሩን አይፈታም ያሉት ሚንስትሯ፤ በመሆኑም የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ኢንመቨስተመንት ለማሰባሰብ የግሉን ዘርፍ ለማሳተፍ ያለውን ውጥን ገልጸዋል።
ለዚህም በሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ ይጀምራል ያሉት ካፒታል ገበያ ላይ መንግስት አይኑን መጣሉን ተናግረዋል። ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ ዳግም የሚጀመረው የኢትዮጰያ የካፒታል ገበያ ለአየር ንብረት ፋይናንስ ገንዘብ ለማሰባሰብ ሁነኛ ሆኖ ታይቷል።
በጉባኤው ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ፋይናንስን ለማሰባሰብ የምታደርገውን ጥረት ገልጸው፤ የሀገሪቱን ለአየር ንብረት የሚስማማ የልማት አጀንዳ ለመደገፍ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
መንግስት ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከያና መቋቋሚያ ከ2011 እስከ 2019 ከሀገር ውስጥና ከውጭ ምንጮች 82 ቢሊዮን ዶላር በመሰብሰብ ኢንቨስት ማድረጉንም ተናግረዋል።