በፔሩ የመንገደኞች አውሮፕላን ከመኪና ጋር ተጋጨ
የመንገደኞች አውሮፕላኑ ለመነሳት በማኮብኮብ ላይ እያለ ከእሳት አደጋ መኪና ጋር ተጋጭቷል
አውሮፕላንና መኪና ግጭት አደጋው የ2 ሰዎች ህይወት አልፏል
በደቡብ አሜሪካዋ ፔሩ የመንገደኞች አውሮፕላን ከመኪና ጋር ተጋጭቶ በሰዎች ላይ ጉዳት አደረሰ።
ከፔሩ አውሮፕላን ማረፊያ በመነሳት ላይ የነበረው የመንገደኞች አውሮፕላን ከእሳት አደጋ መኪና ጋር በመጋጨቱ ነው አደጋው የደረወሰው።
ንብረትነቱ የላትም አየር መንገድ የሆነው የመገደኞች አውሮፕላኑ ለመነሳት በማኮብኮብያው ላይ በመጓዝ ላይ እያለ ነው ከመኪናው ጋር ሊጋጭ የቻለው።
በማህበራዊ ሚዲያዎች የተለቀቁ ቪዲዮዎች አውሮፕላኑ ከመኪናው ጋር ከተጋጨ በኋላ በእሳት ተያይዞ መሬት ላይ ሲንሸራተት ታይቷል።
በአደጋው በእሳት አደጋ መኪና ውስጥ የነበሩ የሁለት ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ፤ እንደ ሰው ደግሞ በአስጊ ሁኔታ ውስጥ መሆኑ ታውቋል።
በመንገደኞች አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ ተሳፋሪዎችም ይሁን የበረራ ሰራተኞች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳልደረሰ የላትም አየር መንገድ በትዊተር ገጹ አስታውቋል።
የፔሩ የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቁ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ እና መጠነኛ ጉዳት የደረሰባቸው 20 ሰዎች ወደ ሆስፒታል ተወስደው ህክምና እየተከታተሉ ነው።
የእሳት አደጋ መኪናው ምን ሊሰራ ወደ ማኮብኮቢያው ገባ የሚለው ግልጽ የሆነ ነገር የለም ተብሏል።