የአለማችን የመጀመሪያዋ በጸሃይ ሃይል የምትሰራ መኪና
“ላይትይር ኦ” መኪና እስከ 70 ኪሎ ሜትር የሚያስጉዝ ሃይልን ከጸሃይ የሚሰበስቡ ፓኔሎች ተገጥመውላታል
ቅይጥ በጸሃይና ኤሌክትሪክ ሃይል የምትሰራው መኪና 262 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ወጥቶላታል
የነዳጅ ዋጋ እየናረ መሄድና የቴክኖሎጂ በየጊዜው መዘመን በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በስፋት ወደገበያ እንዲገቡ እያደረገ ነው።
የኔዘርላንንድስ ኩባንያ ላይትይር ደግሞ በጸሃይ ሃይል የሚሰሩ ተሸከርካሪዎችን ማምረት መጀመሩን ገልጿል።
“ላይትይር ኦ” የሚል ስያሜ የሰጣት መኪና በቀን እስከ 70 ኪሎሜትር የሚያስጉዝ ሃይልን ከጸሃይ የሚሰበስቡ ፓኔሎች ተገጥመውላታል ነው የተባለው።
የሶላር ፓኔሎቹ 60 ኪሎዋት ሃይል ከጸሃይ የሚሰበስቡ ሲሆን፥ ከተሽከርካሪዋ አናት ላይ በልዩ ዲዛይን የተቀመጡ ናቸው።
“ላይትይር ኦ” ከጸሃይ ሃይሏን እየሰበሰበች እስከ 624 ኪሎሜትር ድረስ መጓዝ እንደምትችልም ነው የኢንዲያን ታይምስ ዘገባ የሚያሳየው።
እንደ ኔዘርላንድስ ባሉ በቀን ውስጥ ብዙ ኪሎሜትር የሚሸፍን እንቅስቃሴ በማይደረግባቸው ሀገራት አንድ ጊዜ በተሞላ ቻርጅ ለቀናት “ላይትይር ኦ” ተሽከርካሪን መንዳት እንደሚቻል ኩባንያው ይፋ አድርጓል።
ይሁን እንጂ ኔዘርላንድስ ጨምሮ ጭጋጋማ አየር ለወራት በሚዘልቅባቸው ሀገራት የአዲሷ ተሽከርካሪ የሃይል ምንጭ ጥያቄ ውስጥ መውደቁ አይቀርም።
ፖርቹጋልን በመሰሉ ጸሃይ በማይለያቸው የአውሮፓ ሀገራት እና በአፍሪካ “ላይትይር ኦ” ተፈላጊነቷ እንደሚጨምር ይጠበቃል።
ላይትይር በፊንላንድ በሚገኘው የተሸከርካሪዎች መገጣጠሚያ ማዕከሉ በሳምንት አንድ በጸሃይ ሃይል የምትሰራ መኪናን ማምረት መጀመሩን ገልጿል፤ በ2023 መጨረሻም በሳምንት አምስት “ላይትይር ኦ” ለማምረት ማቀዱን ነው ያስታወቀው።
የላይትይር ኩባንያ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ሌክስ ሆፍስሎት፥ የ“ላይትይር ኦ” ምርት መጀመር አለማችን ከአየር ብክለት ነጻ የማድረግ እንቅስቃሴ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያራምድ ነው ብለዋል።፡
በጸሃይ ሃይል የምትሰራው መኪና 262 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ወጥቶላታል።
“ላይትይር ኦ” የመጀመሪያዋ በጸሃይ ሃይል የምትሰራ መኪና አይደለችም፤ በርካታ የተሽከርካሪ አምራቾች የተለያዩ ዲዛይን ያላቸውን መኪኖች አስተዋውቀዋል። ነገር ግን ወደ ምርት በመግባት የኔዘርላንድሱ ኩባንያ ቀዳሚ ሆኗል።