የማንቸስተር ዩናይትዱ አማካይ ካሴሚሮ የአራት ጨዋታዎች ቅጣት ተጣለበት
የ31 አመቱ ተጫዋች ወደ እንግሊዝ ከመጣ ወዲህ ቀይ ካርድ ሲመለከት ለሁለተኛ ጊዜ ነው
አሰልጣኝ ቴን ሃግ “ዳኝነቱ ወጥነት የጎደለው ነው” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል
በትናንትናው አለት ከሳውዝሀምፕተን ጋር በነበረው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተባረረው ብራዚላዊው የማንቸስተር ዩናይትድ አማካይ ካሴሚሮ የአራት ጨዋታዎች ቅጣት ተጣለበት፡፡
ካሴሚሮ በሳውዝሃምፕተኑ አማካይ ካርሎስ አልካራዝ ላይ በሰራው ጥፋት በጨዋታው ዳኛ አንቶኒ ቴይለር (በቫር የታገዘ ውሳኔ) ቀጥታ የቀይ ካርድ ከሜዳ ሊወጣ ችሏል፡፡
የ31 አመቱ ተጫዋች ከስፔን ወደ እንግሊዝ ከመጣ ወዲህ ቀይካርድ ከሜዳ ሲወጣ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑም ታውቋል።
ባለፈው ወር ማንቸስትር ዩናይትድ ክሪስታል ፓላስን 2 ለ 1 ባሸነፈበት ጨዋታ ቀይ ካርድ ካርድ መመልከቱ አይዘነጋም፡፡
ይሁን እንጅ ካሴሚሮ የተጣለበት ቅጣት የአውሮፓ ጨዋታዎችን ስለማያካትት ክለቡ ዩናይትድ ሀሙስ እለት በዩሮፓ ሊግ ከሪያል ቤቲስ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ የምንመለከተው ይሆናል፡፡
ማንቸስተር ዩናይትድ እና ሳውዝሃምፕተን ጨዋታ ባደረጉት በትናንቱ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ 0 ለ 0 በሆነ አቻ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው፡፡
ከ34ኛው ደቂቃ በኋላ የካሴሚሮን አገልግሎት ማግኘት ያልቻሉት የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ቴን ሃግ ከጨዋታው በኋላ በሰጡት መግለጫ ወጥነት በጎደለው ዳኝነት ደስተኛ አለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡
አሰልጣኙ የካሴሚሮን በቀይ ካርድ ከሜዳ ስለመውጣት ሲናገሩም “ እኔ የማስበው ዳኝነቱ ወጥነት የጎደለው መሆኑ ነው፤ ተጫዋቾች ፖሊሲው ምን እንደሆነ እንኳን አያውቁም” ብለዋል ሲል ስካይ ስፖርት ዘግቧል፡፡
" በአውሮፓ ሊጎች ውስጥ ነው ከ 500 በላይ ጨዋታዎች አድረጎ ቀይ ካርድ ያልተመለከተው ካሴሚሮ በዚህ አጭር ጊዜ እንዴት ሁለት ቀይ ካርድ ሊመለከት ቻለ ?” ሲሉም ጥያቄ አቅርበዋል ቴን ሃግ፡፡
ቴን ሃግ ዩናይትድ በተጨዋቹ ላይ በተሰጠው ውሳኔ ይግባኝ ይጠይቃል ወይ ? ተብሎ ተብሎ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥየቄ "እናያለን" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡