ቀያዮቹ ሰይጣኖችን ለመግዛት ፉክክሩን የተቀላቀሉት ሼክ ጃሲም “ዩናይትድን ወደ ቀደመ ክብሩ እመልሰዋለሁ” ብለዋል
የ2022 የአለም ዋንጫን ያስተናገደችው ኳታር የእንግሊዙን ክለብ ማንቸስተር ዩናይትድ ለመግዛት የሚደረገውን ፉክክር ተቀላቅላለች።
የሀገሪቱ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ልጅ ሼክ ጃሲም ቢን ሃማድ አል ታኒ ዩናይትድን ለመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው አስታወቀዋል።
- ክርስቲያኖ ሮናልዶ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ቅጣት ይጠብቀዋል - ማንቸስተር ዩናይትድ
- ትናንትፓርቹጋላዊው አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በማንቸስተር ዩናይትድ "ተከድቻለሁ" አለ
ምሽትም ቡድኑን ለመግዛት በይፋዊ መንገድ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል ነው የተባለው።
ሼክ ጃሲም የኳታር እስላማዊ ባንክ ሊቀመንበር ሲሆኑ፥ ከፈረንጆቹ 2007 እሰክ 2013 ኳታርን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት ሃማድ ቢን ጃሲም ቢን ጃበር አል ታኒ ልጅ ናቸው።
በእንግሊዝ የሮያል ወታደራዊ አካዳሚ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ሼክ ጃሲም፥ የዩናይትድ ቀንደኛ ደጋፊ መሆናቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን አስነብቧል።
ኳታራዊው ሼክ ጃሲም ዩናይትድን በሜዳም ሆነ ከሜዳ ውጭ ውጤታማ በማድረግ “ወደ ቀደመ ክብሩ” ለመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
“ናይን ቱ ፋውንዴሽን” የተባለው ተቋማቸውም በእግር ኳስ ቡድኖች፣ በስታዲየሞች እና በአጠቃላይ የስፖርት መሰረተ ልማት ላይ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ መዘጋጀቱን ነው ያነሱት።
በፈረንጆቹ 2005 ዩናይትድን በ1 ነጥብ 34 ቢሊየን ዶላር የገዙት የግሌዘር ወንድማማቾች በጥቅምት ወር 2022 ቡድኑን ለመሸጥ መወሰናቸውን ማሳወቃቸው ይታወሳል።
ቡድኑን ለመግዛት ፍላጎት ያላቸው ባለጸጋዎችም እስከ ትናንት ምሽት ጥያቄያቸውን እንዲያስገቡ የተቀመጠው ቀነ ገደብ ተጠናቋል።
ከኳታራዊው ሼክ ጃሲም ባሻገር የእንግሊዙ ቢሊየነር ሰር ጂም ራትክሊፍ ትልቁን ክለብ በእጃቸው ለማስገባት ፉክክሩን ቀደም ብለው ተቀላቅለዋል።
ባለፈው አመት ቼልሲን ለመግዛት ያደረጉት ጥረት ያልተሳካላቸው ሰር ጂም ራትክሊፍ፥ የብሪታንያ ቁጥር አንድ ባለጸጋ ናቸው።
የፈረንሳዩ ኒስ ክለብን የገዙት ራትክሊፍ፥ እንደ ሼክ ጃሲም ሁሉ የዩናይትድ ደጋፊ መሆናቸውን ዘ ሰን ዘግቧል።