የዛሬው የአርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ ጨዋታ የሊጉን ሻምፒዮን ያመላክት ይሆን?
አርሰናል በኢምሬትስ ምሽት 4 ስአት ከ30 ላይ የፔፕ ጋርዲዮላውን ማንቸስተር ሲቲ ያስተናግዳል
መድፈኞቹ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች የጣሉት ነጥብ የምሽቱን ፍልሚያ በከፍተኛ ጫና ውስጥ እንዲያሳልፉ ያስገድዳቸዋል
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ምሽት የሚደረገው የአርሰናልና ማንቸስተር ሲቲ ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ሊጉን በ51 ነጥብ እየመሩ የሚገኙት መድፈኞቹ፥ በ48 ነጥብ የሚከተሏቸውን ሲቲዎች በኤምሬትስ ያስተናግዳሉ። የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላም “ዛሬ የምንገጥመው ምርጡን አርሰናል ነው” ብለዋል።
ጋርዲዮላ የቀድሞው ረዳት አሰልጣኛቸው ማይክል አርቴታ የሰራውን ቡድን ከጨዋታው በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አድንቀዋል።
ስፔናዊው አሰልጣኝ ወደ ኢትሃድ ከመጡ ወዲህ በአርሰናል ተሸንፈው አያውቁም። ከ12 ጨዋታዎች በ11ዱ አሸንፈዋል፤ ባለፉት 5 የኢምሬትስ ግጥሚያዎችም ድል አድርገዋል።
አርሰናል በዚህ የውድድር አመት እስካሁን የተሸነፈው በሁለት ጨዋታዎች ብቻ ነው።
በ21 ግጥሚታዎችም 51 ነጥብ መሰብሰቡ ብርቱ ተፎካካሪነቱን ያሳያል። ይሁን እንጂ የመድፈኞቹ አሁናዊ ብቃት የጋርዲዮላን ለአርሰናል እጅ ያለመስጠት ጉዞ ይገቱታል ወይ የሚለው አጠራጣሪ ነው።
በዚህ አመት በኤፍ ኤ ካፕ ሲቲ 1 ለ 0 ካሸነፈበት ጨዋታ ውጭ ያልተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች የፕሪሚየር ሊጉን መሪነት ለማስቀጠል አልያም በአቻ ነጥብ በጋራ ለመምራት ምሽት ላይ የሚያደርጉት ትንቅንቅ ይጠበቃል።
አርሰናል ከ19 አመት በኋላ ዋንጫውን ለመሳም የሚያደርገው ጉዞን የመወሰን አቅም ያለውን ጨዋታ በድል ለመፈጸም ተዘጋጅተናል ብሏል አሰልጣኙ ሚኬል አርቴታ።
የጋርዲዮላ ረዳት በነበረበት ጊዜ ሁለት ዋንጫዎችን ከሲቲ ጋር ያነሳው አርቴታ፥ መድፈኞቹን ከያዘ በኋላ ከጋርዲዮላ ቡድን ጋር ሰባት ጊዜ ተጋጥሞ በስድስቱ ተሸንፏል።
“ድሉም ሆነ ሽንፈቱ እንደቡድን እንጂ ለአስልጣኞች የሚሰጥ አይደለም” የሚለው አርቴታ “አሁን ትኩረታችን ሲቲን ማሸነፍ ብቻ ነው ማለቱንም ስካይ ስፖርት ዘግቧል።
በፕሪሚየር ሊጉ በ19ኛው ሳምንት በኤቨርተን የተሸፈውና፤ በ20ኛ ሳምንት ከብሬንትፎርድ ነጥብ የተጋራው አርሰናል፥ ማንቸስተር ሲቲን በማሸነፍ ወደ ድል ይመለስ ይሆን?
ሲቲስ በኤምሬትስ የወትሮ የድል ጉዞውን አስቀጥሎ ሊጉን በግብ ክፍያ በልጦ መምራት ይጀምራል? አስተያየታችሁን አጋሩን፡፡