ቴን ሃግ ከ2013 እስከ 2015 ፔፕ ጋርዲዮላ የባየር ሙኒክን አሰልጣኝ በነበሩበት ወቅት አብረዋቸው እንደሰሩ ይታወቃል
ስፔናዊው የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ማንቸስተር ዩናይትድን በመቀየር ኤሪክ ቴን ሃግን አሞግሰዋል፡፡
“ቴን ሃግን ዩናይትዶችን ወደ ቀድሞ ብቃታቸው እየመለሳቸው ለመሆኑ ምልክቶች አሉ" ብለዋል ጋርዲዮላ፡፡
ቴን ሄግ ወደ ማንቸስተር ከመቱ በኋላ ማንችስተር ሲቲን ጨምሮ በተለያዩ ክለቦች ተከታታይ ሽንፈት ቢያስተናግዱም አሁን ላይ የተደሻለ ውጤት በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኙ ሚረር ስፖርት ዘግቧል፡፡
በተለይም በወሩ መጀመሪያ ላይ በማንቸስተር ደርቢ ዩናይትድ በሲቲ 6-3 ከተሸነፈ ወዲህ በሁሉም ውድድሮች በሰባት ጨዋታዎች ሽንፈት ሳያስተናግድ በፕሪምየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ከሻምፒዮኑ በ6 ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ ይገኛል።
በተለይም በስታምፎርድ ብሪጅ ከቼልሲ ጋር ባደረገው ጨዋታ 1-1 በሆነ ውጤት መለያየቱ እንዲሁም ቶተንሃምን በፍጹም በላይነት ማሸነፉ እግር ኳስ አፍቃሪያን አጀማማራቸው ባላማረው ቴን ሃግ ላይ የነበራቸው ተስፋ እንደገና ከፍ እንዲል ያደረገ ነበር፡፡
እንደ ፔፕ ጋርዲዮላ ከሆነ ቴን ሃግ የናይትዶችን ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እየወሰዳቸው ነው፡፡
የሲቲው አሰልጣን ከጨዋታው በፊት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት "ዩናይትድ ተመልሶ እንደሚመጣ ይሰማኛል፤ በመጨረሻም ዩናይትድ ተመልሶ ይመጣል:: የመጀመሪያውን አጋማሽ በቼልሲ ላይ አይቻለሁ፤ በጨዋታው የተመለከትኩት ነገር ወድጄዋለሁ" ብለዋል፡፡
ይህ ብቻ አይደለም ጋርዲዮላ ዩናይትድ በቴን ሀግ መሪነት ጠንካራ ፐሪምየር ሊጉ ተፊካካሪ ክለብ ሆኖ እንደሚመጣ ያላቸው እምነት ገልጸዋል፡፡
ጋርዲዮላ የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ የኦሌ ጉናር ሶልሻየርን ይሰናበታሉ ከተባለበት ወቅት ጀምሮ የአያክሱ ቴን ሃግ ትክክለኛውና ለዩናይትድ የሚመጥኑ አሰልጣኝ መሆናቸው ምክረ-ሃሳብ ሲያቀርቡ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ቴን ሃግ ከ2013 እስከ 2015 ፔፕ ጋርዲዮላ የባየር ሙኒክን አሰልጣኝ በነበሩበት ወቅት አብረው እንደሰሩ ይታወቃል፡፡
ቴን ሃግም ቢሆኑ ከጋረዲዮላ ትልቅ ነገር እንደተማሩና ለፔፕ ያላቸው አድናቆት ከፍተኛ መሆኑ ከቅርቡ የማንቸስተር ደርቢ በፊት በሰጡት መግለጫ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡
“ፔፕን በጣም አደንቃለሁ ፣ ምክንያቱም እሱ ስኬታማ ብቻ ሳይሆን ሰዎችን ወደ እግር ኳስ በሆነ መንገድ የሚስብ ነው” ሲሉም ነበር አድናቆታቸው የገለጹት ቴን ሃግ፡፡