ስማችሁን አጠፈዋለሁ እያለ የሚያስፈራራው ይህ ግለሰብ ከ5 ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ ከባለ ሆቴሎች እንደተቀበለ ተገልጿል
በረሮ እና ያገለገለ ኮንዶም ወደ ታዋቂ ሆቴሎች ይዞ እየገባ በነጻ የሚመገበው ሰው
ጂያግ የሚባለው ሰው የ21 ዓመት ወጣት ሲሆን በቻይናዋ ታይዙ ከተማ ይኖራል፡፡ የዩንቨርሲቲ ተማሪ የሆነው ይህ ወጣት ወደ ተለያዩ ቦታዎች መጓዝ እና መዝናናት ደስታ ይሰጠኛል ብሏል፡፡
ፍላጎቱን ለማሳካትም የገንዘብ እጥረት ስላለበት ሆቴሎችን ለማጭበርበር የተለያዩ ዘዴዎችን ለመከተልም ይወስናል፡፡
ጎብኚ መስሎ ወደ ሆቴሎች የሚገባው ይህ ሰው በሚጓዝባቸው አካባቢዎች በቦርሳው ውስጥ በረሮዎችን ጨምሮ የተለያዩ ነፍሳቶችን ይዞ ሲገባ ነበር ተብሏል፡፡
ከነፍሳት በተጨማሪም ያገለገሉ ኮንዶሞችን ጨምሮ ሌሎች ለሰው ልጆች ንጽህና ችግር የሚፈጥሩ ነገሮችን ሆን ብሎ ክፍል ውስጥ መተው፣ ነፍሳቱን ምግብ ላይ መጨመር እና ሌሎችንም ክስተቶች ሲያደርግ እንደነበር ሳውዝ ቻይና ፖስት ዘግቧል፡፡
የተፈጠሩ ነገሮችን እና የንጽህና ጉድለቶቻችሁን አጋልጣለሁ እያለ ባለ ሆቴሎችን የሚያስፈራራው ይህ ወጣትም በመደራደር በነጻ እንዲመገብ እና ለቀናት ሲዝናና እንደነበር ተገልጿል፡፡
በቻይና የተለያዩ ከተሞች በተመሳሳይ የማታለያ መንገዶች አማካኝነት ባለሆቴሎችን በማስፈራራት ሲያጭበረብር እንደቆየም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ጉዳዩን የተጠራጠረ አንድ የሆቴል ስራ አስኪያጅ ሌሎች ሆቴሎችን ሲጠይቅ ግለሰቡ ሆን ብሎ በነጻ ለመመገብ እና ለመዝናናት በሚል በረሮዎችን እና ሌሎች አጸያፊ ክስተቶችን እንደሚያደርግ ይደርስበታል፡፡
ጉዳዩን ለፖሊስ ካሳወቁ በኋላም ግለሰቡ በህግ ቁጥጥር ስር ውሏል የተባለ ሲሆን በአጠቃላይ 63 ሆቴሎችን ከ5 ሺህ ዶላር በላይ አጭበርብሯል ተብሏል፡፡