ለዓመታት ያለ ስራ ከ16 ተቋማት ደመወዝ ስትቀበል የነበረችው አጭበርባሪ ተያዘች
ግለሰቧ ሳትሰራ ደመወዝ ለዓመታት እንዲከፈላት 50 ተባባሪዎች ነበሯት ተብሏል
እንስቷ ስራ የምትሰራ ለመምሰል ሀሰተኛ ፎቶዎችን እና መረጃዎችን ለአለቆቿ ትልክ እንደነበር ተገልጿል
ለዓመታት ያለ ስራ ከ16 ተቋማት ደመወዝ ስትቀበል የነበረችው አጭበርባሪ ተያዘች።
ጉዋን ዩ የተሰኘችው እንስት በ16 ተቋማት የስራ ቅጥር በመፈጸም ለዓመታት ደመወዝ ስትቀበል ቆይታለች።
ግለሰቧ ለ16 ተቋማት የምትሰራ ብትመስልም ለአንዱም ተቋም ምንም አይነት ስራ እንዳልሰራች ተገልጿል።
የግለሰቧ ዋነኛ ስራ በየተቋማቱ እየተዟዟረች ደመወዝ መሰብሰብ ነበር የተባለ ሲሆን በመጨረሻም በፖሊስ ተይዛለች።
ይህች ቻይናዊት የሽያጭ ሙያተኛ ናት የተባለ ሲሆን ለስራ ቅጥር ቃለ መጠይቅ በሄደችባቸው ቦታዎች ፎቶ እየተነሳች ለተቀጠረችባቸው ተቋማት የሽያጭ ስራ እየሰራች መሆኗን ለማሳየት ስትጠቀምበት ነበርም ተብሏል።
ይህች እንስትም ከ16 ተቋማት ሳትሰራ በተቀበለችው ገንዘብ በሻንጋይ ከተማ ቅንጡ አፓርታማ መግዛቷ ተገልጿል።
ይሁንና ለአንድ የሽያጭ ኩባንያ የስራ መልቀቂያ የጻፈችውን ደብዳቤ ተሳስታ ለሌላ ተቃም መላኳን ተከትሎ በጉዳዩ ጥርጣሬ የገባው ሌላ ኩባንያ ለፖሊስ ያመለክታል።
ፖሊስ በደረሰው የማጭበርበር ጥቆማ መሰረት ከብዙ ክትትል በኋላ ግለሰቧ ያለ ስራ ከብዙ ተቋማት ለዓመታት ደመወዝ እየተከፈላት መሆኑን ይደርስበታል።
በመጨረሻም ይህች እንስት ስራ እንድትቀጠር እና ያለ ልፋት ደመወዝ እንዲከፈላት የሚተባበሩ የጥቅም ተጋሪ የሆኑ 50 ሰዎች እንዳሉም ፖሊስ ገልጿል።
ቻይናዊቷ ለሌላ የስራ ቅጥር ለመፈጸም ቃለ መጠይቅ እያደረገች እያለ በፖሊስ ተይዛ ወደ ማረሚያ ቤት ልትወርድ ችላለች ሲሉ የቻይና ብዙሀን መገናኛዎች ዘግበዋል።
በቻይና በብዙ ተቋማት በመቀጠር ሳይሰሩ ደመወዝ መውሰድ ወንጀል እየተበራከተ መምጣቱ ተገልጿል።