የአፍሪካ ህብረት በኢኳቶሪያል ጊኒ በተከሰተው ፍንዳታ ለተጎዱ ሰዎች ማዘኑን ገልጿል
የአፍሪካ ህብረት በዚህ ፍንዳታ ሳቢያ ለተጎዱ ሰዎች ማዘኑን በህብረቱ ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ መሃማት በኩል ባወጣው መግለጫ አስታዉቋል።
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ኢኳቶሪያል ጊኒ ከትናንት በስቲያ ባታ በተሰኘች የወደብ ከተማ በደረሰው ፍንዳታ የሟቾች ቁጥር ወደ 98 ከፍ ብሏል።ከ600 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ እንደቆሰሉ እና የሟቾች ቁጥር ከዚህም ሊጨምር እንደሚችል ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
ፍንዳታው የደረሰው በሀገሪቱ የንግድ ማዕከል ናት በምትባል ባታ ወደብ ላይ መሆኑ ተገልጿል።የሀገሪቱ የጤና አመራሮች በፍንዳታው ለተጎዱ ዜጎች የደም ልገሳ እንዲያደርጉ ተደጋጋሚ ጥሪ በማቅረብ ላይ ናቸው።
ለፍንዳታው መነሻ ምክንያት ምን እንደሆነ እስካሁን ያልታወቀ ሲሆን በወደቧ አቅራቢያ ያለው ወታደራዊ ቤዝ መነሻ ሊሆን እንደሚችል ሪፖርቶች እየወጡ ነው።