በተለያዩ የመተከል ዞን አካባቢዎች እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን መከላከያ ሰራዊት አስታውቋል
በተለያዩ የመተከል ዞን አካባቢዎች እርምጃ እየተወሰደ ነው-መከላከያ
በመተከል ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ንጹሃንን በሚያጠቁና በሚገድሉ ኃይሎች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን መከላከያ ሰራዊት አስታወቀ፡፡
በሠራዊቱ የ22ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ እና የዞኑ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄነራል ነገሪ ቶሊና እርምጃው ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡
ከአሁን ቀደም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተመራ ልዑክ በተገኘበት በዞኑ በተካሄደው ውይይት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ዞኑ በኮማንድ ፖስት እንዲመራ መደረጉን የገለጹት አዛዡ ሰራዊቱ ቀደም ሲል ችግር በተፈጠረባቸው ቡለንና ወምበራ ወረዳዎች ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ጸረ-ሠላም ኃይሎችን የማደንና እርምጃ የመውሰድ ተግባር እያከናወነ መሆኑን ተናግዋል እንደ ዞኑ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ዘገባ፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ በአመራሩ በኩል የሚታዩ ክፍተቶችን ለመለየት እና በትክክል ለማጥራት የሚያስችሉ የግምገማ መድረኮች በመካሄድ ላይ መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡
ኮማንድ ፖስቱ በዚህ ሂደት ውስጥ እያለ ከትናንት በስቲያ መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም ሌሊት 10 ሰዓት ገደማ በዳንጉር ወረዳ በንገዝ ቀበሌ ጸረ-ሠላም ኃይሎች ገብተው በንጹኃን ዜጎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡
ሠራዊቱ መረጃው እንደደረሰው 11፡40 አካባቢ ወደ ሥፍራው በመድረስ ቀስትና የጦር ማሳሪያ የያዙ 9 የታጠቁ ኃይሎች ላይ እርምጃ መውሰዱንም ነው ብርጋዴር ጄነራሉ የተናገሩት፡፡
ሠራዊቱ በድንጋጤ ወደጫካ የሸሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን የማሰባሰብና የአካባቢውን ደህንነት የመረጋገጥ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ ሸሽተው የሄዱ የጸረ-ሠላም ኃይሎችን በመከታተል ላይ እንደሚገኝም አክለው ገልጸዋል፡፡
እንደ ጄነራሉ ገለጻ ችግሩ ሊያጋጥም እንደሚችል የሚጠቁሙ የተለያዩ ሁኔታዎችን ዋቢ በማድረግ የቀበሌው ሊቀ-መንበር ለዳንጉር ወረዳ የሠላም ግንባታና ጸጥታ ጽ/ቤት መረጃ አስታውቋል፡፡
ሆኖም የጸጥታ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊነቱን ችላ በማለቱና ለጸጥታ ኃይሉ በወቅቱ መረጃ አለማድረሱን ተክትሎ ተገቢው ጥንቃቄ ሳይደረግ በመቅረቱ ጉዳት ሊደርስ ችሏል፡፡
ይህንኑ ተከትሎ ትናንት በተደረገው ግምገማም የጸጥታ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊው በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡