በመተከል ያጋጠመው የጸጥታ ችግር በግድቡ የግንባታ ሂደት ላይ ስጋት ፈጥሮ ነበር ተባለ
በጉባ ወረዳ የተደረገውን የአመራር ሽግሽግ በማስመልከት የስራ መመሪያ ተሰጥቷል
የጸጥታ ኃይሉ “ጉባ ላይ ብዙ መስዋዕትነት” መክፈሉንም ሌ/ጄ አስራት ዴኔሮ ተናግረዋል
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ያጋጠመው የጸጥታ ችግር በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት ላይ ስጋት ፈጥሮ ነበር ተባለ፡፡
ይህ የተባለው በዞኑ ጉባ ወረዳ የተደረገውን የአመራር ሽግሽግ በማስመልከት የስራ መመሪያ በተሰጠበት መድረክ ነው፡፡
በመድረኩ በዞኑ የተቋቋመው የጸጥታ የተቀናጀ ግብረኃይል ዋና ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ ወረዳውን የሚያስተዳድረው አመራር “ድርብ ሃገራዊ ኃላፊነት አለበት” ብለዋል፡፡
አመራሩ ይህን ተገንዝቦ እንዲሰራም ነው ማሳሰቢያ የሰጡት፡፡
አስተባባሪው ወረዳው ትልቁ ሃገራዊ የግንባታ ፕሮጄክት እየተከናወነ ያለበት ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሃገር ሱዳን ጋር የምትዋሰንበት ነው ያሉም ሲሆን “በመተከል ዞን ያጋጠመው የጸጥታ ችግር በግድቡ የግንባታ ሂደት ላይ ስጋት ፈጥሮ” እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ሌተናል ጄኔራሉ “ጉባ ላይ የሚከፈል መስዋዕትነት ትልቅ ነው” ነው ያሉት፡፡ የጸጥታ ኃይሉ በዚህ ወረዳ “ብዙ መስዋዕትነት” መክፈሉን አስታውሰዋል።
በመሆኑም አመራሩ “ጉባ ወረዳን መቀየር የኢትዮጵያን ሕዝብ ሕይወት መቀየር” መሆኑን አውቆ “ከጸጥታ ኃይሉ በመማር” ጉባ ላይ አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት።
እንደ ኢዜአ ዘገባ ከሆነ የወረዳው አገር ሽማግሌዎችና የውይይቱ ተሳታፊዎች በሽግሽጉ ወደ ስራ የመጡት አዳዲስ አመራሮችም ‘ደከመኝ ሰለቸኝ’ ሳይሉ ሁሉንም በአንድ አይን በማየት እንዲያገለግሉ ህዝብ እንዲተባበርም ጠይቀዋል ጄኔራሉ።
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ቡሴና ረጂብ በበኩላቸው በወረዳው ያጋጠመው የጸጥታ ችግር “እየተቃለለ” መሆኑን ተናግረዋል።
የጸጥታ ችግሩ “የሁሉንም ኢትዮጵያዊ አንገት ያስደፋ” ተግባር መሆኑን ጠቅሰው “ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት አመራሩ ይሰራል” ብለዋል።
“ያጋጠመው የጸጥታ ችግር ከአገር አልፎ ቀጠናዊ መልክ ያለው ነው” ያሉት ደግሞ የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ ናቸው።
“እንደ አገር ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ችግር ነው ያጋጠመን” ያሉት አቶ ጋሹ፤ ይህንን መጥፎ ታሪክ ለመቀየር ጠንክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የተቀናጀ ግብረ ኃይሉ እስካሁን በዞኑ ጉባን ጨምሮ ዳንጉር፣ ማንዱራ፣ ወምበራ፣ ቡለንና ድባጤ ወረዳዎች በመገኘት የተደረገውን የአመራር ሽግሽግ ተመልክቷል።